Fana: At a Speed of Life!

ትራምፕ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያውያንን አንድ የሚያደርግ ሊሆን ይገባል – ምሁራን

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በቅርቡ የሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያውያንን የበለጠ አንድ የሚያደርግ እና የተጀመረውን ግድብ ለማጠናቀቅ የሚተጉበት ሊሆን ይገባል ሲሉ ምሁራን ተናግረዋል፡፡
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት ምሁራኑ መሰል በሀገር ሉዓላዊነት ላይ የተቃጡ ድርጊቶችን ኢትዮጵያውያን የውስጥ ችግር ኖሮባቸው እንኳን ተደራድረው አያውቁም ነው ያሉት፡፡
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር የሆኑት ፍሬው ይርጋለም ቁጭት፣ እልህ እና ቂመኝነት የመራው የትራምፕ ንግግር አሜሪካን ከመሰለች የዓለም ጠበቃ እና የዴሞክራሲ ተቆርቋሪ ነኝ ከምትል ሀገር የማይጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አስተያየቱንም የዴፕሎማሲ ቋንቋ ቀለም የራቀው ሲሉ ገልፀታል።
የቀድሞው የኢትዮጵያ አምባሳደር ኢብራሂም እድሪስ በበኩላቸው፥ የትራምፕን አስተያየት ለዘመናት ባልበረደ ፍላጎት እና ጥያቄ 21ኛ ክፍለ ዘመን ላይ ለመጫን የሚሞከር ዘመናዊ እንቅስቃሴ ጋር አመሳስለውታል።
በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሱራፌል ጌታሁን ደግሞ የዶናልድ ትራምፕ ንግግር ከመረዳት እና ከእውቀት ሩቅ መሆንን ያሳየ የሚመስል መሆኑን አንስተዋል፡፡
ምሁራኑ የትራምፕ ቀይ መስመር ማለፍ ምንጭ በኢኮኖሚ ወደኋላ እንደቀረን ማሳያ መሆኑን አውስተዋል፡፡
ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያውያን ያሏቸውን የሃሳብ ልዩነቶች ወደጎን በመተው መረባረብ ይገባቸዋል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ ህዳሴ ግድብን ማጠናቀቅ ከሁሉም የሚጠበቅ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የፕሬዚዳንቱ አስተያየት ለኢትዮጵያውያን አንድነት ማድመቂያ ሲሆን በተባበረ ክንድ ድህነትን ለመጣል የሚተባበሩበት ሊሆን ይገባዋልም ነው ያሉት፡፡
በአፈወርቅ አለሙ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.