Fana: At a Speed of Life!

ከአሽከርካሪ ማሠልጠኛ ተቋማት መካከል 220 ተቋማት ብቻ የተቀመጠላቸውን መስፈርት አሟልተዋል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚገኙት 550 የአሽከርካሪ ማሠልጠኛ ተቋት መካከል 220 ተቋማት የተቀመጠላቸውን መስፈረት አሟልተው አገልግሎት እንደሚሰጡ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ገለፀ።

የትራንስፖርት ሚኒስቴር ከዘርፉ አመራሮች፣ ከአሽከርካሪዎች ማሠልጠኛ እና ተሽከርካሪ ምርመራ ተቋማት ባለሀብቶች ጋር በባህር ዳር ከተማ ውይይት እያካሄደ ነው።

የፌደራል የትራንስፖርት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ምትኩ አስማረ፥ የመንገድ ትራንስፖርት ዘርፍ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ የማህበራዊ ልማት እና የመልካም አስተዳደር እንዲሁም ሠላም ለማስከበር የአንበሳውን ድርሻ ብለዋል።

ይሁን እንጅ ዘርፉ የአሽከርካሪዎች እና የተሽከርካሪ ብቃት አሰጣጥ እንዲሁም የተሽከርካሪ ምርመራ እና የአሽከርካሪዎች ፍቃድ አሰጣጥ ላይ ችግሮች መኖራቸውን አንስተዋል።

በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ከሚገኙት ማሠልጠኛ ተቋማት መካከል 220 ብቻ የተቀመጠላቸውን መስፈርት አሟልተው አገልገሎት እየሰጡ እንደሚገኙም ነው አቶ ምትኩ ያስረዱት።

በተመሳሳይ አገልግሎት እየሰጡ ከሚገኙት 64 ተሽከርካሪ የቴክኒክ ምርመራ ተቋማት 54ቱ የተቀመጠውን መስፈርት አሟልተው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑም ተጠቅሷል።

መስፈርቱን አሟልተው አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትም ቢሆን ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር ስለማይደረግላቸው በስርዓቱ መሰረት የሰውና የሌሎች ግብአቶችን አያሟሉም ነው የተባለው።

በተሽከርካሪ ቴክኒክ ብቃትም ሆነ የአሽከርካሪ ብቃት እና ስነ-ምግባር ችግር ሳቢያ የሚደርሰው የሞት፣ የአካል ጉዳት አደጋ እና የሀብት ውድመት ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝም ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

በናትናኤል ጥጋቡ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.