Fana: At a Speed of Life!

በዚህ አመት ሊጠናቀቁ የሚገባቸው ፕሮጀክቶች በምንም ምክንያት መተላለፍ የለባቸውም – ወይዘሮ አዳነች

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 23 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2013 ዓ.ም የመንግስት ስራዎች መሪ እቅድ ዙሪያ ዛሬ በአዳማ ከተማ ምክክር እያደረገ ነው።

በምክክር መድረኩ ላይ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ፣ የአዲስ አበባ ብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙን ጨምሮ ሌሎች የከተማ አስተዳደሩ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች ውይይቱን ሲያስጀምሩ በመዲናዋ በዚህ አመት የሚጠናቀቁ 1 ሺህ ፕሮጀክቶች እንዳሉ አንስተዋል።

አመራሩ እነዚህን ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅና ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በቁርጠኝነት እንዲሰራም አጽንኦት ሰጥተዋል።

አዳዲስ የተመደቡም ሆኑ ነባር አመራሮች የፖለቲካ እና የመንግስት ስራዎችን ሳይቀላቀሉ እንዲያከናውኑም ጠይቀዋል።

ያለፉ ስህተቶችን በማረም በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች የተቀመጡ ግቦችን በማሳካት ረገድ አመራሩ የተጣለበትን ሀላፊነት ሊወጣ ይገባልም ነው ያሉት፡፡

ኮቪድ 19ኝን የመከላከል፣ የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ፣ የኑሮ ውድነትን መቀነስ እና የተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻል ትኩረት የሚደረግባቸው ስራዎች መሆናቸውንም አብራርተዋል።

የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ የከተማዋን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ ረገድ አመራሩ በትጋት ሊሰራ ይገባልም ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮች በቀጣይ በትኩረት በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረው ምክክር እስከ ነገ ድረስ ይቀጥላል።።

የአዲስ አበባ ከተማ ብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ አለሙ በበኩላቸው በውይይቱ ወደ መዋቅሩ አዲስ የተቀላቀሉ ኃላፊዎች በየተመደቡበት ተቋም የከተማዋን አስተዳደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታ ለመቀየር ስለሚወጡት ኃላፊነት፣ በዋና ዋና ግቦችና የትግበራ ስልቶች ላይ የጋራ ግንዛቤ ለመያዝናየአመለካከትና የተግባር አንድነትን ለመፍጠር የጎላ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል ።

በፋሲካው ታደሰ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.