Fana: At a Speed of Life!

የምክር ቤቱ አባላት ህወሓትን ጨምሮ ህገ ወጥ መሳሪያ ታጥቀው የዜጎችን ህይወት በማጥፋት ላይ ያሉ ቡድኖች በሽብርተኝነት ሊበየኑ ይገባል አሉ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 24 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ህወሃትን ጨምሮ ህገ ወጥ መሳሪያ ታጥቀው የዜጎችን ህይወት በማጥፋት ላይ ያሉ ቡድኖች በሽብርተኝነት ሊበየኑ እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አነሱ።

ምክር ቤቱ ዛሬ በመደበኛነት ከያዛቸው አጀንዳዎች አስቀድሞ በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ግፍና ጭፍጨፋ ላይ ውይይት አድርጓል።

ምክር ቤቱ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን ማንነትን መሰረት ያደረገው ጭፍጨፋ ላይ የተሰማውን ሀዘን በመግለፅ እና የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማድረግ መደበኛ ውይይቱን ሊያደርግ ቢያስብም አባላቱ ቅድሚያ ሊሰጥ የሚገባው የዜጎች ህይወት በመሆኑ ውይይቱ ከዚህ እንዲጀምር በሚል በጉዳዩ ላይ በስፋት ተወያይቷል።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤው አቶ ታገሰ ጫፎ ምክር ቤቱ አጀንዳውን ቀድሞ ቀርፆ የተዘጋጀ መሆኑን በመጥቀስ በዜጎች ላይ የተፈፀመውን ጥቃት በሚመለከት ትናንት ማምሻውን የምክር ቤቱ አመራር ምክክር አድርጎበት አስፈፃሚው አካል ማብራሪያ እንዲሰጥበት ውሳኔ ላይ መደረሱን አንስተዋል፡፡

ይህንን ተከትሎሞ በጉዳዩ ላይ የምክር ቤቱ አባላት ሀሳብ እንዲሰጡበት ተደርጓል።

በዚሁ መሰረት ህወሃትን ጨምሮ ጥቃት የሚፈፅሙ ህገ ወጥ ቡድኖችን በሽብርተኝነት በመበየን የማያዳግም እርምጃ እንዲወሰድባቸው የሚል ሀሳብ ቀርቧል።

ምክር ቤቱ በጉዳዩ ዙሪያ በስፋት ከተወያየ በኋላ አስፈፃሚው አካል ምክር ቤት ቀርቦ ማብራሪያ እንዲሰጥ፣ ምህረት የሌለው እርምጃ እንዲወሰድ እና ችግሩ እንዳይደገም ምን መወሰን አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ የውሳኔ ሀሳብ እንዲቀርብ አቅጣጫ አሳልፏል።

በተጨማሪም ዛሬ ምክር ቤቱ የግልግል ዳኝነትና የእርቅ አሰራር ስርአትን ለመደንገግ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ በዋናነት ለህግ ፍትህ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመራ ሲሆን፥ በአጋዥነት ለውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ኮሚቴ መርቶታል፡፡

ከዚህ ባለፈም የግብርና አምራችና አስመራች ግንኙነትን ለመወሰን የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ለግብርና አርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡

የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ረቂቅ አዋጅንም ምክር ቤቱ ለሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል፡፡

እንዲሁም የተጓደሉ የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችን ምክር ቤቱ የመደበ ሲሆን በዚህም የገቢ፣ እድገትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ በመሆን ወይዘሮ ያየሽ ተስፋሁን፣ የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደግሞ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ እንዲሁም የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አአቶ አቡ ብርቂ ሆነው ተመድበዋል፡፡

በሀይለኢየሱስ ስዩም እና በአፈወርቅ አለሙ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.