Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ ሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ የደንብ አገልግሎት ቁጥጥር ኦፊሰሮችን አስመረቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ለሁለት ወራት ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ 761 የደንብ አገልግሎት ቁጥጥር ኦፊሰሮችን በዛሬው ዕለት አስመርቋል።

ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ቡልቡላ መደበኛ ፖሊስ ማሰልጠኛ በመገኘት ለደንብ ማስከበር ኦፊሰሮች የስራ መመሪያ ተሰጥተዋል።

ወይዘሮ አዳነች ኦፊሰሮቹ በከተማዋ የሚስተዋለውን የህግ ጥሰት በተለይ ህገወጥ የመሬት ወረራ እና ግንባታ፣ የጎዳና ላይ ንግድ በመከላከል አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችሉ መሆኑን ገልጸዋል።

የከተማዋ ልማት ሊፋጠን የሚችለው ህግና ስርዓት ሲከበር ነው ያሉት ምክትል ከንቲባዋ÷ ኦፊሰሮቹ በስልጠናው ያገኙትን ልምድ ወደ ስራ ሲገቡም ህብረተሰቡን በጥሩ ስነምግባር፣ በታማኝነት እና በትህትና ማገልገል ይገባቸዋል ብለዋል ።

በከተማዋ ህግና ስርዓት እንዲከበር ለሚደረገው ጥረት ሁሉ የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ወይዘሮ አዳነች ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ኮሚሽነር አዱኛ ደበላ በበኩላቸው÷ በከተማዋ የሚስተዋሉ ህገወጥ ተግባራት ዘርፈ ብዙ ጉዳት እያስከተሉ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ የሚያከናውናቸውን የልማት ስራዎች ለማደናቀፍ የሚደረጉ ህገወጥ ድርጊቶችን የመከላከል እና የመቆጣጠር ስራ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ለአራተኛ ጊዜ ካሰለጠናቸው ከ2 ሺህ 761 የደንብ ማስከበር ኦፊሰሮች መካከል 1ሺህ 44ቱ ሴቶች መሆናቸውን ከአዲስ አበባ አስተዳደር ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.