Fana: At a Speed of Life!

ዶ/ር አብረሃም በላይ በምዕራብ ወለጋ ዞን በዜጎች ላይ በደረሰው ጥቃት ማዘናቸውን ገለፁ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 24 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብረሃም በላይ በምዕራብ ወለጋ ዞን በዜጎች ላይ በደረሰው ጥቃት ማዘናቸውን ገለፁ፡፡

ዶክተር አብረሃም በፌስ ቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ “በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ በሚኖሩ ወገኖች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ስሰማ እጅግ የከፋ ሐዘንና ድንጋጤ ተሰምቶኛል ብለዋል”።

ዘመኑ እውቀትና ቴክኖሎጂ የተስፋፋበትና ዓለም የተቀራረበችበት ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ በዚህ የቴክኖሎጂ ዘመን የሰውን ልጅ አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶች ማድነቅና መደመም እንዲሁም ለመጋራትና ለመጠቀም መሽቀዳደም እንጂ የሰው ልጅን ሰው በግፍና በጭካኔ ሲገድለው መስማትና ማየት እጅጉን ልብ ይሰብራል ብለዋል።

አጥፊዎች የጥፋት በትራቸውን ለማንሳት የቱንም ያክል ሰበብ ቢደረድሩም ከሕግና ከሞራል ተጠያቂነት አያመልጡምም ነው ያሉት።

በዚህ የውድድር ዘመን የሚያስፈልገው ትብብር እና ፉክክር እንጂ ግድያና መጠፋፋት አልነበረም ያሉት ሚኒስትሩ በግድያና መጠፋፋት ማንም አካል አትራፊ አይደለም ሲሉም ገልጸዋል።

ከዚህ የጥፋትና የበቀል አዙሪት መውጣት እንዲቻል መንግስትና ሕዝብ ሕግና ስርዓትን ለማስፈን በትብብር መስራት አለባቸው ብለዋል።

አጥፊዎችና ከጥፋቱ ለማትረፍ የተሰማሩ አካላት ካለፈ ጥፋታቸው ተምረው ወደማያባራና የታሪክ ተጠያቂ ከሚያደርግ የሴራ ተግባር እጃቸውን እንዲሰበስቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዚህ ማንነት ላይ የተመሰረተ ጥቃት ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች ሰላማዊ እረፍት እና ለሁሉም ሃገር ወዳድ ዜጎች መፅናናትን ተመኝተዋል፡፡

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.