Fana: At a Speed of Life!

የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ምጣኔ እየሰፋ ቢሄድም ዜጎች የመከላከያ መንገዶችን እየተገበሩ አይደለም

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 24 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ምጣኔ እየሰፋ ቢሄድም ዜጎች አሁንም የመከላከያ መንገዶችን በተገቢው ሁኔታ እየተገበሩ አለመሆኑን የኦሮሚያ እና ደቡብ ክልል ጤና ቢሮዎች አስታወቁ፡፡
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ደረጉት በኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ የድንገተኛ አደጋ ቁጥጥር እና የጤና ምርምር ዳይሬክተር አቶ ገመቹ ሹሜ እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት በክልሉ የሚስተዋለው የቫይረሱ ሥርጭት ሁኔታ አሳሳቢ ነው፡፡
እንደ አብነትም እየተካሄደ ካለው አነስተኛ የምርመራ አቅም አንጻር ቫይረሱ የሚገኝባቸውና ለህልፈት የሚዳረጉ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ለስርጭቱ መባባስም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳቱን ተከትሎ በጤና ሚነስቴር የወጣውን መመሪያ ዜጎች ተግባራዊ አለማድረጋቸው ዋና ምክንያት መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
የደቡብ ክልለ ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ አቅናው ካውዛ በበኩላቸው፥ አሁን ላይ የሚስተዋለው ከፍተኛ የስርጭት ምጣኔ ሶስቱን የመከላከያ ህጎች ካለመተግበር የመጣ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡
ከዜጎች መዘናጋት ባለፈም የመንግስት አካላት የሚያሳዩት ቸልተኝነት አሁን ላይ ቫይረሱ በሀገሪቱ የሌለ አስመስሎታል ነው የሚሉት፡፡
በቀጣይ ችግሩን ለመቅረፍ ከህግ አስፈጻሚ አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል፡፡
የምርመራ አቅምን ማሳደግ አንዱ መፍትሄ መሆኑን ያነሱት ባለሙያዎቹ ከመመርመሪያ ኪት አቅርቦት እጥረት ጋር ተያይዞ የምርመራ አቅሙ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል ዝቅተኛ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም የሚመለከታቸው አካላት ናሙና ከመሰብሰብ እና ከመላክ እንዲሁም ባለሙያን ከማበረታታት አንፃር የሚያሳዩት ቸልተኝነት ችግሩን አሳሳቢ አድርጎታልም ነው የሚሉት፡፡
ዜጎች በቀጣይ ለከፋ ችግር ከመዳረጋቸው በፊት የመከላከያ መመሪያዎችን እንዲተገብሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.