Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ የፈጠራ ውጤቶችን ሥራ ላይ ለማዋል ቪዛ እና ስቴምፓወር በጋራ መስራት የሚያስችል አጋርነት ፈጠሩ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 24 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ የፈጠራ ውጤቶችን ሥራ ላይ ለማዋል ቪዛ እና ስቴምፓወር የተባሉ ድርጅቶች በጋራ ለመስራት የሚያስችል አጋርነት ፈጠሩ።

ሁለቱ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ቅንጅት መፍጠራቸውን በዛሬው ዕለት ይፋ አድርገዋል።

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የትምህርት ሚኒስትር ደኤታ ሚሊዮን ማቲዎስ፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ደኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱን ጨምሮ ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

ስቴምፓወር በኢትዮጵያ ባለፉት 13 ዓመታት 43 ማዕከላት የከፈተ ሲሆን ÷ በማዕከላቱ ተማሪዎች በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግና ሂሳብ ችሎታቸውን  የሚያጎለብቱበት ፕሮጀክት ቀርጾ  ሲተገብር ቆይቷል።

በማዕከላቱ የፈጠራ ሥራዎችን ይዘው የሚመጡ ተማሪዎች ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን የቴክኒክ፣ የስልጠና እና አጋር በማፈላለግ ድጋፍ እንዲያገኙ የማመቻቸት ስራዎች እየተሰሩም ነው ተብሏል።

የቴምፓወር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቅድስት ገብረአምላክ ÷ድርጅቱ ቪዛ ከተሰኘው ተቋም ጋር በመተባበር የፈጠራ ሥራ ያላቸውን ልጆች ወደ ተግባር የሚቀይሩበት መርሃ ግብር ቀርጾ እንቅስቃሴ ጀምሯል ብለዋል።

መርሃ ግብሩ ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የሚተገበር ሲሆን የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችና ሥራ ፈጣሪዎች የሚደግፍ መሆኑን አብራርተዋል።

በመርሃ ግብሩ መሰረት ቪዛ የተሰኘው ተቋም የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን የፈጠራ ሥራ ያላቸው ዜጎች ከገንዘብ አስተዳደር፣ አያያዝና የአዕምሮ ውጤታቸውን በምን መልኩ ሥራ ላይ ማዋል አለባቸው? የሚለው ላይ የክህሎት ስልጠና ይሰጣቸዋልም ነው ያሉት።

የፈጠራ ውጤቱን ሥራ ላይ ለማዋል ከባለሃብቶች ጋር ማገናነት ሌላው ተግባር ነው ያሉት ሥራ አስፈጻሚዋ የፈጠራ ባለቤቶቹ ፍቃድ እስኪያገኙ ድረስም ድጋፋችን አይቋረጥም ብለዋል።

መርሃ ግብሩ እስኪጠናቀቅ ድረስ 4 ሺህ የፈጠራ ባለቤቶችን ለማሰልጠን እቅድ ተይዟል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የጾታ፣ እድሜና  የትምህርት ደረጃ ከግምት ውስጥ የማይገባ መሆኑን ጠቅሰው ዋናው የሚፈለገው ፈጠራው ስራ ላይ ሊውል የሚችል መሆኑ ብቻ ነው ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት የዲጂታል ኢኒሼቲቭ አስተባባሪ ሜሪየም ሰኢድ በበኩላቸው÷ ተቋማቱ የፈጠሩት አጋርነት ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ከማገዝ ባለፈ ለወጣቶች ሥራ እድል ፈጠራ አወንታዊ ሚና ይኖረዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.