Fana: At a Speed of Life!

ሕወሓት በትግራይ በሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ላይ ጥቃት አድርሷል – ጠ/ሚ ዐቢይ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 25 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሕወሓት በትግራይ በሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ላይ ጥቃት ማድረሱን አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፌስ ቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ ሰሜን ዕዝን ለመዝረፍም ሙከራ ማድረጉን አስታውቀዋል።

ይህ ሠራዊት ከሃያ ዓመታት በላይ የትግራይን ሕዝብ ሲጠብቅ የቆየ ሠራዊት መሆኑን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ አላማው በቦታው የሚገኘውን የትግራይን ሕዝብ ከጥቃት ለመከላከል ያለመ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሕወሐት ግን እንደ ባዕድና እንደ ወራሪ ሀገር ሠራዊት ቆጥሮ፤ የመከላከያ ሠራዊቱን ለመምታትና ለመዝረፍ ተነሥቷልም ነው ያሉት።
በዚህ በዳልሻሕ በኩልም ጦርነት ከፍቷል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ።

መንግሥት የትግራይ ሕዝብ እንዳይጎዳ በማሰብ፣ ጦርነት እንዳይፈጠር የትእግሥቱ ጫፍ ድረስ ታግሷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጦርነት የሚቀረው ግን በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ እንዳልሆነም ጠቁመዋል።

የመከላከያ ሠራዊቱም በኮማንድ ፖስት እየተመራ ሀገሩን የማዳን ተልዕኮውን እንዲወጣ ትዕዛዝ እንደተሰጠውም አስታውቀዋል።

ቀዩ መሥመር የመጨረሻው ነጥብ መታለፉን በማውሳትም ሀገርና ሕዝብ ለማዳን ሲባል ኃይል የመጨረሻው አማራጭ ሆኗልም ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነገሮችን በሰከነ መንፈስ እንዲከታተል፣ በየአካባቢው ሊከሠቱ የሚችሉ ትንኮሳዎችን በንቃት እንዲቃኝና ከመከላከያ ሠራዊት ጎን እንዲቆምም ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.