Fana: At a Speed of Life!

ለድንገተኛ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ጠንካራ ምላሽ የማይበገር የጤና ስርዓትን መገንባት ተጠናክሮ ይቀጥላል – ዶክተር ሊያ ታደሰ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2013 (ኤፍቢሲ) የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ለድንገተኛ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ጠንካራ ምላሽ የማይበገር የጤና ስርዓትን መገንባት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጹ፡፡
 
ሚኒስትሯ ይህንን ያሉት በ2ኛው የጤናው ዘርፍ ጉባዔ በአዲስ አበባ በተካሄደበት ወቅት ነው፡፡
 
ሚኒስትሯ ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር ባለፉት አምስት ዓመታት የመጀመሪያው የጤናው ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሲተገበር መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡
 
የዕቅዱ ትግበራ ውጤታማነትንም ለመገምገም በተካሄዱ ጥናቶችና ዳሰሳዎች የተቀመጡ ግቦችን ሙሉ በሙሉ ማሳካት ባይቻልም ሃገሪቱ በዕቅድ ዘመኑ ያጋጠሟትን ተግዳሮቶች በመቋቋም በጤናው ዘርፍ ወደታለመው የልማት ግብ ለመድረስ ውጤታማ ስራ መሰራቱንና በትክክለኛ አቅጣጫ ላይ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡
 
ዶክተር ሊያ ለውጤቱ መገኘት ምክንያት የሆኑትንም ሲጠቅሱ ለዕቅዱ ማስፈጸሚያ የተቀረጹትን አራቱን የጤና ትራንስፎርሜሽን አጀንዳዎችን ትኩረት ሰጥቶ መተግበር በመቻሉ ነው ብለዋል፡፡
 
በተለይም የወረዳ ትራንስፎርሜሽን፣ የመረጃ አብዮት፣ የጤና አገልግሎት ጥራትና ጥራትና ፍትሃዊነትን ለማምጣትና ሩህሩህ፣ ተገልጋይ አክባሪና ተንከባካቢ የጤና ባለሙያዎችን ማፍራትን ለማሳካት በትኩረት መተግበሩም ለውጤቱ መገኘት ምክንያት መሆኑ ነው የጠቀሱት፡፡
 
ባለፈው ዓመት የዕቅድ ማጠናቀቂያ ዓመት ላይ የተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዘርፉ ለማስመዝገብ ከታለመለው ግብ ለመድረስ በአንዳንድ ፕሮግራሞች ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ተናግረዋል፡፡
 
በሌላ በኩል በጉባዔ ላይ በጤናው ዘርፍ የላቀ አስተዋጽዖ ላበረከቱ ባለሙያዎችና አመራሮች እውቅና አግኝተዋል፡፡
 
በዚህም መሰረት ዶክተር መኮንን አይችሉህም፣ አቶ ደምሴ ደኔቦ እና ዶክተር ከይረዲን ረዲ በህይወት ዘመን የላቀ የሙያ አገልግሎት፣ አቶ በሃይሉ ታደሰ፣ ዶክተር ከፍያለው ታዬ እና አቶ አለማየሁ ግርማ በሙያ መስክ የላቀ ስራና አገልግሎት እንዲሁም በተለያዩ የስራ ሃላፊነቶች የላቀ አመራርነት ደግሞ ወይዘሮ ኑሪያ የሱፍ፣ ዶክተር ይገረሙ ከበደ እና ዶክተር ሻሎ ዳባ የዕውቅናና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል፡፡
 
ባለፉት ዓመታት በጤናው ዘርፍ ከባለሙያነት አንስቶ እስከ ከፍተኛ አመራርነት ሲያገለግሉ የነበሩ ዶክተር ከበደ ወርቁንም ልዩ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
 
በተጨማሪም በኮቪድ 19 መከላከልና መቆጣጠር አስተዋጽኦ ላደረጉ ለሁሉም ክልልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በማገልገል ላይ በሚገኙ የጤና ባለሙያዎችና ሰራተኞች ስም የምስጋና የእውቅና ሽልማት እንደተበረከተላቸው ከሚኒስቴሩ ያገነነው መረጃ ያመለክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.