Fana: At a Speed of Life!

የሶማሌ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች የሀገሪቱንና የክልሉን ሰላም ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ገለፁ

አዲስ አባበ ፣ ጥቅምት 27 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ እና የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ በወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳይ ዙሪያ ከሶማሌ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች ጋር ተወያዩ።
በውይይቱ ላይ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ መስጠፌ መሀመድን ጨምሮ ሌሎች የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አደም ፋራህ ከሀዲው የህወሀት ቡድን ባለፉት 27 አመታት በክልሉና በሀገሪቱ ህዝብ ላይ ሲያደርሰው ከነበረው አስከፊ ጉዳት ባለፉት ሶስት አመታት በሀገሪቱ የተረጋገጠውን ለውጥ ለማደናቀፍ በተለያየ የጥፋት ተግባር ላይ ተሰማርቶ እንደነበረ ተናግረዋል።
መንግስት የአጥፊዎችን እኩይ ሴራ በሆደ ሰፊነት ሲያልፍ መቆየቱን የጠቆሙት አፈጉባኤው ህወሃት ከሰሞኑ በትግራይ ክልል በሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የሰነዘረው ጥቃት መንግስት በሀገር አፍራሹ ህወሃት ላይ እርምጃ እንዲወስድ እንዳስገደደው ተናግረዋል።
መላው የሶማሌ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በመገንዘብ መንግስት እየወሰደ የሚገኘውን እርምጃ እንዲደግፉና የሀገሪቱን እና የክልሉን ሰላም ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አፈ ጉባኤው ጥሪ አቅርበዋል።
የገንዘብ ኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ በውይይቱ ላይ ወቅቱ የክልሉ ህዝብ አንድነቱን በማጠናከር፤ በክልሉ ከሚኖሩና ከክልሉ አዋሳኝ ክልል ህዝቦች ጋር ሰላማዊ አብሮነቱን ማጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።
የክልሉንና የሀገሪቱን ሰላም ማረጋገጥ የሚሰራበት ወቅት በመሆኑ የክልሉ የሀገር ሽማግሌዎች አስተዋጽኦዋቸውን እንዲያጎለብቱ ጠይቀዋል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የሀገር ሽማግሌዎች በህወሃት ውስጥ ያለ ቡድን በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የሰነዘረው ጥቃት መቼም ታሪክ የማይረሳው የሀገር ክህደት መሆኑን ጠቁመው መንግስት በአጥፊው ቡድን ላይ እየወሰደ የሚገኘውን እርምጃ እንደሚደግፉት ተናግረዋል።
የሀገር ሽማግሌዎቹ ከመንግስት ጎን ሆነው የሀገርና የክልሉን ሰላም አጠናክረው ለማስቀጠል መዘጋጀታቸውን ማረጋገጣቸውን ከሶማሌ ክልል ቴሌቪዥኝ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.