Fana: At a Speed of Life!

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በትግራይ ክልል የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ በሙሉ ድምጽ ወሰነ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 28 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል ጣልቃ እንዲገባ እና ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ያቀረበው የውሳኔ ሃሳብ በሙሉ ድምጽ ፀደቀ፡፡

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የፌደራል መንግስቱ በትግራይ ክልል ጣልቃ እንዲገባና ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም የውሳኔ ሃሳብ አቅርቧል፡፡

ከዚህ ባለፈም የትግራይ ክልል ምክር ቤት እና ስራ አስፈጻሚ ታግዶ የሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር አስፈጻሚውን የመምራት እና ምርጫ የማካሄድ ሃላፊነት እንደሚሰጠው በውሳኔ ሃሳቡ ተቀምጧል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ክልሉ ስላለበት ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየሶስት ወሩ ለምክር ቤቱ ሪፖርት እንዲያቀርቡ የሚለውም ተካቷል፡፡

በስብሰባውም በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ላይ ተወያይቶ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል፡፡

ህገ ወጥ ቡድኑ ለሃገር ሰላም ፀር እና አደገኛ በመሆኑ ሁኔታዎችን ለማረጋጋት የውሳኔ ሃሳቡ መፅደቁ ተገልጿል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት ውሳኔው ተገቢና ወቅታዊ በመሆኑ ተፈጻሚ መሆን ይገባዋል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ቡድኑ ሃገር እንዳትረጋጋ እና በሰላም እጦት እንድትማቅቅ እየሰራ በመሆኑ ከልክ ያለፈ ትዕግስት ያሳየው የፌደራል መንግስት በአስቸኳይ ተፈጻሚ እንዲያደርገውም ጠይቀዋል፡፡

በሃብታሙ ተክለስላሴ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.