Fana: At a Speed of Life!

በህወሓት ቡድን ላይ ህግን ለማስከበር እየተወሰደ ያለውን እርምጃ እንደግፋለን – የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) መንግሥት በአጥፊው የህወሓት ቡድን ላይ ህግን ለማስከበር እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፉ ከአስሩ ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌችና የሃይማኖት አባቶች ገለፁ።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ላይ ከሀገር ሽማግሌዎችና ሃይማኖት አባቶች ጋር በትናንትናው እለት በአዳማ ከተማ ውይይት አካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የተሳተፉ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች፥ ሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን በትግራይ ክልል የሚያካሂደውን የሕገ መንግስት ጥሰት ለማስቆም በየጊዜው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሲወስዳቸው የነበሩ እርምጃዎችና ውሳኔዎችን አስመልክቶ አስፈላጊውን ግንዛቤ ማግኘታቸውን ገልፀዋል።

ሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን ከእኩይ ተግባራቱ እንዲመለስ የተሰጠውን ዕድል ካለመጠቀሙም በላይ ከህዝቡ ጎን ቆሞ ህዝባዊ ወገንተኝነትን እየተወጣ ባለው የሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊት ላይ አሳፋሪና ታሪክ ይቅር የማይልለትን ተግባር መፈፀሙንም አስታውቀዋል።

ጥቃቱ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የተፈፀመ በመሆኑ የሀገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን በመወከል ባለ 5 ነጥብ የአቋም መግለጫ ማውጣታቸውንም ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በአቋም መግለጫቸውም፥ የፌደራሉ መንግሥት ህገ ወጡ የህወሐት ቡድን ህገ መንግስቱንና የህግ የበላይነትን አክብሮ እንዲንቀሳቀስ ከበቂ እንዲሁም ልዩነቶችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ በውይይትና በሃሳብ ልዕልና መፍታት እንዲችል በቂ ዕድል ቢሰጠውም ጥቃት ወደ መፈፀም በመግባቱ መንግሥት እየወሰደ ያለውን ርምጃ እንደሚደግፉ ገልፀዋል።

የትግራይ ህዝብን እንዲሁም የሀገሪቱን ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት የማስከበር ተልዕኮ ይዞ ሌት ከቀን ራሱን መስዋዕት እያደረገ ባለው የሰሜን ዕዝ መከላከያ ሠራዊት ላይ ከሃዲ፣ ጽንፈኛና የእናት ጡት ነካሽ አጥፊው የህወሓት ቡድን የፈፀመውን እኩይና አስነዋሪ ጥቃት እንደሚያወግዙም አስታውቀዋል።

መንግሥት በዚህ ከሃዲ ቡድን ላይ ሕግንና ሥርዓትን እንዲሁም የህገ መንግስቱን የበላይነት ለማስከበር እየወሰደ ያለውን አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ እንደሚደግፉና ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙም አረጋግጠዋል።

እንዲሁም በግንባር እየተዋደቀ ላለው የመከላከያ ሰራዊት በስንቅና ትጥቅ፣ በሰው ሀይልና በደም ልገሳ ጭምር ህዝቡ ከመንግስት ጎን እንዲቆም ለማድረግ እንደሚሰሩም ገልፀዋል።

ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓለዊነት ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በግንባር ቀደምትነት ሲዋደቅ የኖረው የትግራይ ሕዝብ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን፣ እናቶችና ወጣቶች አሁን በትግራይ ክልል እየተቋቋመ ካለው ጊዜያዊ አስተዳደርና የፀጥታ ኃይሎች ጎን በመሰለፍ የኢትዮጵያን አንድነት ለማስከበርና ሰላሟን ለማስጠበቅ ከፌደራል መንግስት ጎን እንዲሰለፉም ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.