Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ ወጣቶች የከተማዋን ሰላም ለማስጠበቅ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አስታወቁ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 1 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሀገርን የማፍረስ አጀንዳ ይዘው የሚንቀሳቀሱ አካላት ሰለባ ሳይሆኑ የከተማዋን ሰላም ለማስጠበቅ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ገለጹ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ አስተባባሪነት ከተለያዩ ከፍለ ከተሞች የተውጣጡ ወጣቶች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል፡፡

ወጣቶቹ በውይይቱ ላይ የህወሓት የጥፋት ቡድን በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው ጥቃት አሳፋሪ እና የሀገር ክህደት ተግባር በመሆኑ በፅኑ እናወግዛለን ብለዋል፡፡

ሀገርን የማፍረስ አጀንዳ ይዘው በህብረተሰቡ ውስጥ የተሰገሰጉ አካላትን ተልዕኮ ሰለባ ባለመሆን፣ የሚሸርቡትን ሴራ በማጋለጥ የከተማዋን ሰላም ለማስጠበቅ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡም ነው የተናገሩት።

የፌደራሉ መንግስት የወሰደው እርምጃ ትክክለኛ እና ጊዜውን ያገናዘበ ነው ያሉት ወጣቶቹ፥ ከሀገር መከላከያ እና ከጸጥታ አካላት ጎን በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከንቲባ የህዝብ አደረጃጀት አማካሪ አቶ ሺሰማ ገብረስላሴ በበኩላቸው÷ የጥፋት ቡድኑ የተሰጡትን መልካም ዕድሎች ከመጠቀም ይልቅ የሀገር ሉዓላዊነት እና የህዝብን ደህንነት አደጋ ላይ ጥሏል ነው ያሉት፡፡

አያይዘውም ወጣቶቹ በጽንፈኛው የህወሓት ቡድን በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ የተሳሳቱ መረጃዎችን ባለመቀበል ከአካባቢያቸው ሳይርቁ ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የአካባቢያቸውን ሰላምና ጸጥታ በመጠበቅ የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት አለባቸው ማለታቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕሬስ ሰክሬታሪያት ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.