Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ ወድቆ የተገኘ ቦምብ ፈንድቶ በአንድ ግለሰብ ላይ ቀላል የአካል ጉዳት ማድረሱን ፓሊስ ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 2፣ 2013 (ኤፍቢሲ) በአዲስ አበባ አድዋ ድልድይ ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ ቦምብ ፈንድቶ በአንድ ግለሰብ ላይ ጉዳት መድረሱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ዛሬ ጠዋት ሁለት ሰዓት አካባቢ ድርጊቱ መፈጸሙንም ነው ኮሚሽኑ ያስታወቀው፡፡

ግለሰቡ ቀላል ጉዳት የደረሰበት ሲሆን በሚኒልክ ሆስፒታል የህክምና ክትትል እየተደረገለት ይገኛል፡፡

የታክሲ ረዳት የሆነው ግለሰብ ወደ ሥፍራው ለመፀዳዳት ባመራበት ወቅት በማዳበሪያ የተጠቀለለ እቃ ተመልክቶ በእግሩ ከነካካው በኋላ ፈንድቶ ግለሰቡ ራሱን እንደሳተ ነው ለፖሊስ የገለጸው፡፡

የህገ-ወጡ ህወሓት ቡድን ተላላኪዎች በመዲናዋ የጥፋት ተግባር ለመፈፀም ያዘጋጇቸው የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች በህብረተሰቡ ጥቆማና በፀጥታ ኃይሉ ክትትል መያዛቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውሷል፡፡

ኮሚሽኑ በተለያዩ ሥፍራዎች በህዝቡ ላይ ጉዳት ለማድረስ በማቀድ ልዩ ልዩ የጦር መሳሪያዎችን በመጣል ጉዳት ሊያደርሱ ስለሚችሉ ህብረተሰቡ ባለማወቅ ራሱን ለአደጋ እንዳያጋልጥና አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ መልዕክት ማስተላለፉን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.