Fana: At a Speed of Life!

አዲሱ የበጀት ቀመር ለፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል የላቀ ሚና አለው – የፌዴሬሽን ምክር ቤት

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሀገሪቷ አሁን ለደረሰችበት የኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት ፍላጎትን መሰረት ያደረገ የበጀት ቀመር ተግባራዊ መደረጉ ለፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል የላቀ ሚና እንዳለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አደም ፋራህ ገለጹ።

ምክር ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዲሱ የበጀት ቀመር አስተዳደር፣ አተገባበር፣ የበጀት ክፍፍል መረጃ አያያዝና አጠቃቀም ዙሪያ በአዳማ ዛሬ እየመከረ ነው።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ እንደገለፁት፥ ከክልል መንግስታት ገቢና የወጪ ፍላጎት ጋር የተጣጣመ የበጀት ቀመር ተግባራዊ ተደርጓል።

የመድረኩ ዓላማ የቀመሩ አስተዳደርና አተገባበር ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ አንፃር እየተተገበረ መሆኑን ለመገምገም መሆኑንም ተናግረዋል።

ይህም ጤናማና ውጤታማ የበጀት ድጎማ ቀመር እንዲኖር ከማድረጉም ባለፈ ዘመን ተሻጋሪ ሆኖ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።

በስራ ሂደትም በየጊዜው እየተተገበረና ውጤታማነቱ አየተገመገመ ይሄዳል ያሉት አፈ ጉባኤው፥ ክልሎች ፍትሃዊ የገቢ ክፍፍል እንዲኖራቸው ለማስቻል በ2012 ዓ.ም ተግባራዊ መደረጉን ነው የተናገሩት።

በዚህም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ትግበራ ጥሩ ውጤት መገኘቱን የገለጹት አፈ-ጉባኤው፤ “ይሄም በክልሎች መካከል ፍትሃዊና የተመጣጠነ ልማት እንዲረጋገጥ ያስችላል” ብለዋል።

የፌዴራል መንግስት ለክልሎች የሚሰጠው የበጀት ድጎማ ቀመር ውጤታማነትን ለማረጋገጥ የመረጃ አያየዝና አጠቃቀም ወሳኝ መሆኑንም ነው የገለጹት።

“ለዚህም ወቅታዊ፣ ትክክለኛና ጥራት ያለው የመረጃ አደረጃጀትና አያያዝ ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል” ነው ያሉት፡፡

በመረጃ አያያዝ፣ አቀራረብና አጠቃቀም ሊኖር የሚችለውን ክፍተት ለማስወገድ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥናት እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።

በ1989 ዓ.ም የነበረውን የበጀት ድልድል ቀመር ከአጠቃላይ በጀት 70 በመቶ የሚሆነው ለፌደራል 30 በመቶ ለክልሎች ድጎማ የሚሰጥ ሲሆን አዲሱ ቀመር 50 በመቶ ለፌደራል፤ 50 በመቶ ደግሞ ለክልሎች እንደተሰጠ መገለፁን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.