Fana: At a Speed of Life!

የኮሚሽነሮች እጩ አቅራቢ ኮሚቴ ስራውን በይፋ መጀመሩ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 4፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የኮሚሽነሮች እጩ አቅራቢ ኮሚቴ ጋር ባካሄዱት ውይይት ኮሚቴው ስራውን በይፋ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

አፈ-ጉባኤ የኮሚሽኑን አደረጃጀት እና አሰራር ለማሻሻል ቀጣይ ውይይት ይካሄዳልም ብለዋል፡፡

በምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት እና በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በጋራ የሚሰሩትን ስራዎች ለማሳለጥ እንዲቻል በቀጣይ ጽህፈት ቤቱ በምክር ቤቱ ውስጥ ከተቋቋመ በኋላ ከሰብዓዊ መብት ከሚሽን መስሪያ ቤት አንድ ባለሙያ ተመድቦ ስራውን እንዲጀምርም ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ በበኩላቸው የቀረበውን ሪፖርት መነሻ በማድረግ በመመዘኛዎች እና በመመሪያዎች ላይ ማሻሻያ መደረግ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

የጠቅላይ ፍርድቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ በበኩላቸው በእጩነት የሚቀርቡ ግለሰቦች በትምህርት ዝግጅት ብቁ የሆኑ እና ለህገ-መንግስቱ ተገዢ መሆን እንዳለባቸው በማሻሻያው መካተት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ በተቋሙ በርካታ የመዋቅር ለውጦች እየተደረጉ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም መመዘኛ መስፈርቶቹ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን አስረድተው ከውይይቱ የተነሳውን ሀሳብ መደገፋቸውንም ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.