Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ወጣቶች ማህበር ጠቅላላ ጉባኤ በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 19፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአማራ ወጣቶች ማህበር ለሁለት ተከታይ ቀናት የሚቆይ ጠቅላላ ጉባኤውን በዛሬው እለት በባሕር ዳር ከተማ ማካሄድ ጀመረ።

የአማራ ወጣቶች ማኅበር 5ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ‹‹አንደነት ለአማራ ወጣቶች ውበት፤ ለኢትዮጵያ ድምቀት›› በሚል መሪ ቃል ነው በመካሄድ ላይ የሚገኘው።

በውይይቱ ከአማራ ክልል እና ከሁሉም አካባቢ የተወጣጡ ወጣቶች፣ የሌሎች ክልል ወጣት ማህበራት ተወካዩች እና የአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ወጣች ተወካዮችም በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

በውይይት መድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ርዕስ መስተዳደድ ልዩ አማካሪ አቶ ጎሹ እንዳላማው፥ ከ1960 ዓ.ም ጀምሮ ለነበረው ለውጥ የወጣቶች ንቅናቄ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን ለመጣው ለውጥም የወጣቶች ትግል ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፤ ይሁን እንጂ ለውጡ አሁንም ፈተናዎች አሉበት፤ የሚፈለገው ለውጥ እንዲመጣ የሀገራችን መፃኢ እድል በወጣቶች እጅ ላይ ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል ወጣቶች ማህበር ሊቀ መንበር ወጣት አባይነህ መላኩ በበኩሉ፥ የአማራ ወጣቶች ማህበር ከተመሠረተበት 1995ዓ.ም  ጀምሮ  ከመንግስትና ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የአባላትንና የሌሎች ወጣቶችን የማህበራዊ ኢኮኖማያዊና ፓለቲካዊ ችግሮች ለመቅረፍ በርካታ ስራዎችን እየሠራ መሆኑን  ገልጸዋል፡፡

ማህበሩ 884 ሺህ ነባር እና 30ሺህ አዲስ አባላት ይዞ እየተንቀሳቀስ እንደሚገኝ አስረድተው፤ ማህበሩ በክልሉ ከማንኛውም  የፓለቲካ ጣልቃ ገብነት፣  ከዘር፣ ከሃይማኖትና ፓለቲካ አመለካከት ነፃ መሆኑንም አስታውቋል።

የወጣቶች ማህበር በቀጣይ የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን አንድነት እና ሠላም ለማጠናከር በትኩርት ከሌሎች የሀገሪቱ ወጣቶች ጋር በመሆን እንደሚሰራ ተገልጿል።

በናትናኤል ጥጋቡ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.