Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ መኮንን ከቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቮሶግሉ ጋር በስልክ ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 6፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቮሶግሉ ጋር በስልክ ተወያዩ።

ውይይታቸውም በትግራይ እየተካሄደ ባለው ህግ የማስከበር ዘመቻ ዙሪያ መሆኑንም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በዚሁ ወቅት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፥ የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል እየወሰደ ባለው ህግን የማስከበር ዘመቻ ዙሪያ ገለፃ አድርገዋል።

በዚህም የህወሓት ጁንታ ቡድን በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መፈፀሙን እና የጦር መሳሪያዎችን ለመዝረፍ ሙከራ ማድረጉን አስረድተዋል።

የህወሓት ጁንታ ቡድን ተግባርም ወንጀል ብቻ ሳይሆን የሀገር ሉዓላዊነትን መዳፈር እንደሆነም ገለፃ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት አሁን እያካሄደ ባለው ዘመቻም የወንጀለኛው የህወሓት ጁንታ ቡድን አባላትን ለህግ ማቅረብና በክልሉ የሀግ የበላይነትን ለማስከበር እንደሆነም አስታውቀዋል።

የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቮሶግሉ በበኩላቸው፥ የቱርክ መንግስት የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል ህግን ለማስከበር ያሳለፈውን ውሳኔ ይገነዘባል ብለዋል።

መንግስት በክልሉ እየወሰደ ያለው ህግን የማስከበር ዘመቻ የሲቪሎች ደህንነት ባስጠበቀ መልኩ በአጭር ጌዚ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ያላቸውን እምነትም ገልፀዋል።

በመጨረሻም አቶ ደመቀ መኮንን የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሆነው በመሾማቸው የእንኳን ደስ አለዎት መልእክትም አስተላልፈዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.