Fana: At a Speed of Life!

ከሁመራና አካባቢዋ ተሰደው የነበሩ ነዋሪዎች ሠላም በመስፈኑ ወደ ቀዬአቸው እየተመለሱ ነው

አዲስ አበባ፣ ህዳር 7፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሁመራና አካባቢዋ በነበረው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ሰግተው ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ተሰደው የነበሩ ነዋሪዎች ሠላም በመስፈኑ ወደቀዬአቸው መመለሳቸውን ተናገሩ።

ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን በሰሜን ዕዝ አባላት ላይ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ መንግስት ቡድኑን ለፍትህ ለማቅረብ ያለመ የሕግ ማስከበር ዘመቻ እያካሄደ ይገኛል።

በዚህ ዘመቻ በርካታ የትግራይ አካባቢዎች ከሕገወጡ የህወሓት ቡድን አገዛዝ ነጻ እየወጡ ነው።

ነጻ በወጡ አካባቢዎችም የአገር መከላከያ ሠራዊት ሠላምና መረጋጋት የማስፈን ስራ እያከናወነ ይገኛል።

በሁመራና አካባቢዋ ሲካሄድ በነበረው የሕግ ማስከበር እርምጃ በመስጋታቸው ወደተለያዩ አካባቢዎች ተሰደው የነበሩ ነዋሪዎች ወደቀዬአቸው መመለስ ጀምረዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች በነበረው የተኩስ ልውውጥ ምክንያት በፍርሃት ቀዬውን ትተው ተሰደው እንደነበር ለኢዜአ ተናግረዋል።

አሁን የአገር መከላከያ ሠራዊት አካባቢውን በመቆጣጠሩ ያለምንም ስጋት መመለስ እንደቻሉም ገልጸዋል።

በሰሜን ዕዝ የ23ኛ ክፍለ ጦር አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ሻምበል ፈረደ በበኩላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ንብረት ተጠብቆ ለባለቤቶቹ እየተመለሰ መሆኑን ተናግረዋል።

አካባቢው አሁን ወደ ቀድሞ ሠላሙ መመለሱንም ስለመናገራቸው ኢዜአ ዘግቧል።

መንግስት በትግራይ ክልል እየወሰደ ባለው ሕግ የማስከበር ዘመቻ ሁመራን ጨምሮ በርካታ ከተሞች በአገር መከላከያ ቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወቃል።

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.