Fana: At a Speed of Life!

ፅንፈኛው የህወሓት ቡድን ለህግ እስከሚቀርብ ድረስ ህግን የማስከበር ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል – አቶ ብናልፍ አንዷለም

አዲስ አበባ፣ ህዳር 8፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያን ለማፈራረስ መከላከያን ማፍረስ የሚል ዓላማ ይዞ የተነሳው ፅንፈኛው የህወሓት ቡድን ለህግ እስከሚቀርብ ድረስ ህግን የማስከበር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብናልፍ አንዷለም ተናገሩ።
“ለሀገር መከላከያ ክብር እቆማለሁ” በሚል በጽህፈት ቤቱ በተካሄደው መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት አቶ ብናልፍ፥ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት በጁንታው የህወሓት ቡድን አስነዋሪ ጥቃት መፈጸሙን አውስተዋል፡፡
በንግግራቸውም ህወሓት በዓለም ታሪክ ለዓመታት የጠበቀውን የራሱ ሰራዊት ላይ ጥቃት የፈጸመ የእናት ጡት ነካሽ ቡድን መሆኑንም ገልጸዋል።
አቶ ብናልፍ “በዛሬው መርሐ ግብር ላይ ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ ለሚገኘው ሰራዊት አጋርነትን የምናሳይበትና ክብር የምንሰጥበት ነው” ብለዋል።
እንዲሁም “በህዝብና በመንግስት የተሰጣቸውን ግዳጅ ሲወጡ በጁንታው የህወሓት ቡድን ክህደት የተሰው የመከላከያ ሰራዊት አባላትንም የምንዘክርበት ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
አያይዘውም ይህ እኩይ ድርጊት ከተፈጸመበት ጊዜ አንስቶ እስከአሁኑ ሰዓት ድረስ ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከዳር እያወገዙት መሆኑንና ይህ ቡድን ለፍርድ እስከሚቀርብ ድረስ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ መናገራቸውን ከፓርቲው ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.