Fana: At a Speed of Life!

ብልጽግና ፓርቲ የተሳተፈበት የቻይና እና የአፍሪካ ሀገራት ገዥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት በቪዲዮ ኮንፈረንስ ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 8 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ብልጽግና ፓርቲ የተሳተፈበት የቻይና እና የአፍሪካ ሀገራት ገዥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት በቪዲዮ ኮንፈረንስ ተካሄደ።

በቻይና የኮሚኒስት ፓርቲ አዘጋጅነት የተካሄደው የቻይና አፍሪካ ገዥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት የብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ ከ25 በላይ የአፍሪካ ሃገራት የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሳተፉበት ውይይት ነበር ።

በውይይቱ የቻይና እና የአፍሪካ ሀገራት ግንኙነት በቀጣይ ተጠናክሮ ስለሚቀጥልበት ሁኔታ ምክክር ተደርጎበታል፡፡

የአፍሪካ ሀገራት ፖለቲካ ፓርቲዎች ከቻይና ጋር በነበራቸው ግንኙነት መጠቀማቸውንና ግንኙነታቸውን አጠናክረው መቀጠል እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡

የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ያለውን ግንኙነት በቀጣይ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚፈልግ አስታውቋል፡፡

ቻይና በባለፉት ሁለት አስርት አመታት ከፍተኛ የሚባል ስኬት ማስመዝገቧ ተገልጿል፡፡

የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስትር ሶንግ ታው እንደገለጹት÷ ቻይና በቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ መሪነት ባለፉት አመታት በተለያዩ ዘርፎች ስኬቶችን ማስመዝገቧን ተናግረዋል፡፡

በተለይ በድህነት ቅነሳ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጅ በመሰረተ ልማትና በሌሎች የተለያዩ ዘርፎች ከፍተኛ ስኬት ማስመዝገባቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

700 ሚሊየን የቻይና ህዝብን ከድህነት አረንቋ ማላቀቃቸውን ለአብነት መነሳቱን ተጠቁሟል።

የአፍሪካ ሀገራት ከቻይና ስኬት መማር አለባቸው ያሉት ሚኒስትሩ በቀጣይ የአፍሪካ ሀገራት ለሚያከናወኑት የድህነት ቅነሳና ሌሎች ስራዎች የቻይና መንግስት ድጋፍ እንደማይለያቸው አረጋግጠዋል፡፡

በውይይቱ የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የቀጣይ አምስት አመታት እቅድ ለተሳታፊዎቹ መቅረቡን ከብልፅግና ፓርቲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በአፍሪካ ሀገራት ሲከሰት ቻይና የአፍሪካ ሀገራትን ለመርዳት ያደረገችው አስተዋጾ ከፍተኛ እንደነበር የውይይቱ ተሳታፊዎች አንስተዋል፡፡

በዚህ ረገድ በተለይ ኢትዮጵያ ከቻይና ለአፍሪካ ሀገራት የተደረገውን የኮቪድ 19 መከላከያ ቁሳቁሶችን ለየሀገራቱ በማከፋፈል ረገድ ላደረገችው አስተዋጽኦ የውይይቱ ተሳታፊዎች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.