Fana: At a Speed of Life!

መንግስት በትግራይ እየወሰደ ያለው ህግን የማስከበር እርምጃ መሆኑን በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ለኖቤል የሰላም ሽልማት ኮሚቴ አስታወቁ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ እያካሄደ ያለው ህግን የማስከበር እርምጃ መሆኑን በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ለኖቤል የሰላም ሽልማት ኮሚቴ አስታወቁ።
መቀመጫቸውን ኖርዌይ ያደረጉ 28 ኢትዮጵያውያን ምሁራን የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ ለኖቤል የሰላም ሽልማት ደብዳቤ አስገብተዋል።
ኢትዮጵያውያኑ በደብዳቤያቸው፥ መንግስት በህወሃት ፅንፈኛ ቡድን ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ በተመለከተ በዓለም አቀፍ ሚዲያ ተቋማት የሚነገሩ መረጃዎች የተሳሳቱ እና መሰረተ ቢስ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ምሁራኖቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ የተለያዩ ማሻሻያዎች ሲያደርጉ መቆየታቸውን ጠቅሰው፤ ማሻሻያዎቹ የሚታይ ለውጥ ማምጣታቸውን አብራርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ሰላም እና መረጋጋትን ለማምጣት ሲሰሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ተቋርጦ የቆየውን የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት እንዲታደስ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።
ይሁን እንጂ ይህንን ለውጥ ላለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያን ለራሱ በሚመቸው መንገድ ሲመራ የቆየው ፅንፈኛው የህወሓት ቡድን ለውጡን ለማደናቀፍ እና ከመንግስት በተቃራኒ በሆነ መልኩ ሲሰራ መቆየቱን አስታውቀዋል።
ከዚህ ባለፈም እራሱን በትግራይ ክልል በመሸሸግ ለጦርነት ሲዘጋጅ እና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ግጭቶች እንዲቀሰቀሱ እና ሀገሪቱ እንዳትረጋጋ በማህበራዊ ትስስር ድረ ገፆች የተለያዩ የሀሰት ፕሮፖጋንዳዎችን ሲነዛ መቆቱንም ጠቅሰዋል።
እንዲሁም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለታጣቂዎች በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ድጋፍ በማድረግ ግጭቶች እንዲቀሰቀሱ በዚህም ሀገር እንዳትረጋጋ እና የንፁሃን ህይወት እንዲጠፋ፣ ጉዳት እንዲደርስ፣ ዜጎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ እንዲሁም የንብረት ውድመት ማድረሱንም ለአብነት ጠቅሰዋል።
ኮቪድ 19ን ተከትሎ በሀገሪቱ ምርጫ ቢራዘምም፤ የህወሓት ፅንፈኛ ቡድን ግን ከሀገሪቱ የምርጫ ቦርድ እውቅና ውጪ በክልሉ ህገ ወጥ ምርጫ ማካሄዱንም ገልፀዋል።
በተጨማሪም ህወሓት እኔ ከሌለው ሀገር ትፈርሳለች በሚል የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ሲነዛ መቆየቱንም ነው ምሁራኑ ያነሱት።
ይህንን ተከትሎም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራን እና መላው ህዝብ መንግስት ዋነኛ ስራው የሆነውን ህግ እና ስርዓትን የማስከበር ስራ እንዲሰራ ጥሪ ማቅረባቸውን አውስተው፤ ለሆነው ሁሉ መንግስት የትችት ዋና ማእከል መሆኑን አንስተዋል።
የኖቤል የሰላም ኮሚቴ ሰላም በአንድ ወገን ጥረት ብቻ አይመጣም ማለቱን በማስታወስም መንግስትም ጉዳዩን በሆደ ሰፊነት ሲመለከት መቆየቱን እና በሽምግልና ለመፍታት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱንም አስታውቀዋል።
ይሁን እንጂ ህገ ወጡ የህወሓት ቡድን ይህንን ሁሉ በማለፍ በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኘው የሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ድንገተኛ ጥቃት መፈፀሙን አስረድተዋል።
ይህንን ጥቃት መፈፀማቸውንም የፓርቲው ከፍተኛ አመራር በሆኑት አቶ ሴኩቱሬ ጌታቸው አማካኝነት ማመናቸውንም ነው የጠቀሱት።
መንግስትም ህወሓት የፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ ወደ ህግ የማስከበር ዘመቻ ተገዶ መግባቱንም ነው የገለፁት።
ሆኖም ግን አንድ አንድ ዓለም አቀፍ የዜና አውታሮችም መንግስት በትግራይ ክልል እየወሰደ ያለው የህግ የማስከበር እርምጃ በትግራይ ላይ የተከፈተ ጦርነት እንዲሁም የእርስ በእርስ ግጭት አስመስለው እየዘገቡ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል።
ምሁራኑ በደብዳቤያቸው በትግራይ ክልል እየተካሄደ ባለው ህግ የማስከበር ዘመቻ ዙሪያ ሆን ተብለው የተፈበረኩ አሳሳች መረጃዎች ለኮሚቴው ሲደርሱ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል።
ስለሆነም እኛ በኖርዌይ የምንኖር ኢትዮጵያውያም ምሁራን የኖቤል ሰላም ኮሚቴው እየተወሰደ ያለው ግህ የማስከበር እርምጃ እንጂ ጦርነት አለመሆኑን ሊገነዘብ እንደሚገባ አጽኖት ሰጥተዋል።
አሁን መንግስት እየወሰደ ያለው ህግ የማስከበር ዘመቻ ግልፅ እና የሚሳካ አላማ ያለው መሆኑንም ነው ያነሱት።
ነገር ግን ከህግ ማስከበር ዘመቻው ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ መንግስት እና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ላይ የሚቀርቡ ውንጀላዎች ሀሰተኛ እና መሰረት የሌላቸው ነው ብለዋል ምሁራኑ በደብዳቤያቸው።
የኖቤል የሰላም ኮሚቴም መንግስት በትግራይ ክልል እያካሄደ ያለው ህግን የማስከበር ዘመቻ መሆኑን እንዲረዳም ጠይቀዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.