Fana: At a Speed of Life!

ሬውተርስና ቢቢሲን ጨምሮ የተሳሳቱና ሚዛናዊነት የጎደላቸው ዘገባዎችን በመሥራት የቀጠሉ መገናኛ ብዙኃን መኖራቸው ተጠቆመ

አዲስ አበባ ፣ህዳር 15 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሬውተርስና ቢቢሲን ጨምሮ የተሰጣቸውን ሙያዊ አስተያየት ችላ በማለት የተሳሳቱና ሚዛናዊነት የጎደላቸው ዘገባዎችን በመሥራት የቀጠሉ የውጭ የመገናኛ ብዙኃን መኖራቸውን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ ለአዜአ በላከው መግለጫ የውጭ መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎቻቸው እውነት ላይ የተመሰረቱ ሚዛናዊና ተአማኒነት ያላቸው ብሎም ሙያዊ ሥነ ምግባር የተላበሱ እንዲሆኑ የሚረዳ ግብረ መልስ እንደሚሰጥና የእርምት ዕርምጃ እንደሚወስድ ገልጿል።
በዚህ ረገድ መሻሻሎችን ማየት ቢቻልም የተሰጣቸውን ሙያዊ አስተያየት ችላ በማለት የተሳሳቱ ወይም ሚዛናዊነት የጎደላቸውን ዘገባዎች በመሥራት የቀጠሉ አንዳንድ የውጭ የመገናኛ ብዙኃን መኖራቸውን አስታውቋል።
የተሳሳተ ወይም ሙያዊ ሚዛናዊነት የጎደለው ዘገባ ከሚሰሩት መካከልም ሬውተርስ፣ ቢቢሲ (አማርኛና እንግሊዝኛ ፕሮግራሞች)፣ የጀርመን ድምጽ የአማርኛ ፕሮግራም እንዲሁም አልጀዚራ (እንግሊዝኛ) ተጠቅሰዋል፡፡
“የተጠቀሱት መገናኛ ብዙኃንና ህጋዊ ፈቃድ የሌላቸው እንደ አዲስ ስታንዳርድ ያሉ ድረ-ገፆች ብሎም የጋዜጠኝነት ዕውቅናና ፈቃድ የሌላቸው እንደ ዊሊያም ዴቪሰን ያሉ ግለሰቦች በቅርቡ የፌዴራል መንግስትና የሀገር መከላከያ ሰራዊት በህወኃት ጁንታ ላይ ህግን ለማስከበር የሚያካሂደውን ዘመቻ በተመለከተ የተዛባ መረጃ ሲሰጡ ነበር” ብሏል።
በዚህም ከሀቅ የራቁ መረጃዎችን የማሰራጨት፣ የኢትዮጵያ መንግስትን አስተያየት ያለማካተት፣ ዘመቻው የእርስ በርስ ጦርነት እንደሆነ አስመስሎ የማቅረብ እና እየተወሰደ ያለውን ሕጋዊ ዕርምጃ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሰላም ኖቤል ሽልማት አሸናፊነት ጋር በማያያዝ ሃሰተኛ መረጃ እያሰራጩ እንደሚገኝ ባለስልጣኑ ገልጿል።
የፌደራል መንግስቱ ተገዶ የገባበት ሳይሆን ችግሩን በሰላምና በድርድር የመፍታት ፈቃደኝነት የጎደለው በማስመሰል እንዲሁም ሊፈጠር የሚችለውን ሰብዓዊ ቀውስ በተጋነነ መልኩ በመሳል ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲፈጥር የማድረግ አዝማሚያ መታየቱንም ነው የጠቆመው።
“የተጠቀሱት ዘጋቢዎች የሚያሰራጯቸው መረጃዎች ዓለም አቀፍ የጋዜጠኝነት መርሆዎችን ያላገናዘቡ እና የግል አቋም የመያዝ አዝማሚያ የሚታይባቸው ናቸው” ብሏል ባለስልጣኑ በላከው መግለጫ።
በመገናኛ ብዙሃኑ ላይ ሚዛናዊነትን አለመጠበቅ፣ እውነትን መርህ ያላደረጉ ዘገባዎች፣ በርዕሰ-አንቀጾቻቸው ላይ ግነትን መጨመር፣ የመንግስት አስተያየትን አለማካተትና ሙያዊ ስነ ምግባር ያለመላበስ ችግር በተለዩት መገናኛ ብዙሃን ላይ እንደሚታይባቸውም ጠቅሷል።
በተጨማሪም ዘመቻው ከህግ ማስከበር ሂደት ይልቅ የእርስ በርስ ጦርነት አንድምታ ላይ ማተኮርና የችግሩን ስፋት መለጠጥ የተሳሳቱና ሚዛናዊነት የጎደላቸው ዘገባዎችን በመሥራት የቀጠሉ መገናኛ ብዙኃን ብሎ በለያቸው ላይ የሚታይ የጋራ ችግር እንደሆነ ባለስልጣኑ አመልክቷል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.