የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከ8 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 16 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ያገኘውን ግምታቸው ከ8 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ የሆኑ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረገ።
በዚህም ከ400 በላይ የሆኑ ዊልቸሮችን፣ ከዘራ፣ ክራንችና የእጅ መደገፊያ፣ ዘይት፣ ዱቄት፣ፓስታ፣ መኮረኒ እንዲሁም የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ለክልሎችና ለከተማ አስተዳደሮች አከፋፍሏል፡፡
ከተገኘው የገንዘብ ድጋፍ ውስጥ 5 ሚሊየን ብር ከዩኒሴፍ ኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል የተገኘ ሲሆን ይህም ለሴክተሮችና ለአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ለቁሳቁስ ግዢ የዋለ መሆኑ ተገልጿል፡፡
መቀመጫውን አሜሪካ ሀገር ካደረገው አጋፔ ሞቢሊቲ ኢትዮጵያ ከተሰኘ ግብረሰናይ ድርጅት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያገኘውን ግምቱ 3 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር የሆነውን ድጋፍ ለአማራ፣ ለኦሮሚያ፣ ለቢኒሻንጉል፣ ለጋምቤላ፣ ለአፋር፣ ለሲዳማ ክልሎች እና ለሁለት ከተማ አስተዳደሮች አስረክቧል፡፡
በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽን እያደረሰ ያለውን አሉታዊ ጉዳት በመገንዘብ ችግሩን በዘላቂነት ለመቋቋምና ለመቀነስ ዩኒሴፍ ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡
አጋቤ ላደረገው ድጋፍም ምስጋና አቅርበው የኮሮና ወረርሽኝ ከሀገሪቱ እስከሚጠፋ ድረሰ መሰል ድጋፎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ማቅረባቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ተወካይ ቪንቶስ ቪንሲን በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያ መንግስት ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡
ዩኒሴፍ በዚህ ረገድ ድጋፍ እንደያሚደርግና በተለይም ህጻናት፣ አካል ጉዳተኞች፣ ነፍሰ ጡርና የሚያጠቡ እናቶችን ማገዝ የሚያስችል ድጋፎችን ያደርጋልም ነው ያሉት፡፡