Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ከህወሓት ጋር ግንኙነት ላላቸውና የባንክ ሂሳባቸው ለታገደባቸው ድርጅቶች በጥሬ ገንዘብ እንዲከፈላቸው የሚያደርጉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳሰበ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 16 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ከህወሓት ጋር ግንኙነት ላላቸውና የባንክ ሂሳባቸው ለታገደባቸው ድርጅቶች በጥሬ ገንዘብ እንዲከፈላቸው የሚያደርጉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳሰበ፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሽብር ጥቃት እና ዘርን መሰረት ያደረገ ሁከት እና ብጥብጥ እንዲነሳ በማድረግ ሂደት ውስጥ እንዲሁም ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል ለመናድ በተፈጸመ ህገ-ወጥ ተግባር ውስጥ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ በወንጀል ተግባር ተሳትፈዋል በሚል ተጠርጥረው ምርመራ የተጀመረባቸው ከህወዓት/ ትህነግ ጋር ግንኙነት ያላቸው 38 ድርጅቶች መታገዳቸው ይታወቃል፡፡

ይሁንና የድርጅቶቹ የባንክ ሂሳብ መታገዱን ተከትሎ ለድርጅቶቹ ገቢ የሚሆኑ ገንዘቦች በባንክ በኩል መከፈሉ ቀርቶ በእጅ ለእጅ ወይም በካሽ (በጥሬ ገንዘብ) እንዲከፈላቸው የሚጠይቁ እና የሚቀበሉ የታገዱ ድርጅቶች አመራሮች እና ክፍያውን በዚሁ መልክ የሚፈጽሙ ግለሰቦች እና ተቋማት እንዳሉ ደርሰንበታል፡፡

ድርጊቱ የምርመራ ስራውን የሚያደናቅፍ፣ ለግብር ስወራ ወንጀል ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር እና ከብሄራዊ ባንክ መመሪያ ድንጋጌዎች ጋርም የሚጋጭ እና በህግ የሚያስጠይቅ ተግባር በመሆኑ የድርጅቶቹ አመራሮች እና ሰራተኞች እንዲሁም በዚሁ መልክ ክፍያዎችን እየፈጸማችሁ ያላችሁ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ከድርጊታችሁ እንድትቆጠቡ እያሳሰብን በድርጊቱ የሚሳተፉ ግለሰቦችን እና ድርጅቶችን በምርመራ አጣርተን በህግ እንዲጠየቁ የምናደርግ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

በመሆኑም ማንኛውም ወደታገዱት ድርጅቶቹ ገንዘብ ገቢ ማድረግ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው በባንክ በኩል እንዲፈጽም እያሳሰብን የሚኖሩትን ጥያቄዎች እና ጥቆማዎች ለተቋማችን ማቅረብ የሚችል መሆኑን አክለን እናሳውቃለን፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.