Fana: At a Speed of Life!

ያለንበት ምእራፍ የተጀመሩ የልማት፣ የሰላምና የስርዓት ግንባታ ስራዎች ማስቀጠል የሚያስፈልግበት ነው- አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 17፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) “ያለንበት ምእራፍ የተጀመሩ የልማት፣ የሰላምና የስርዓት ግንባታ ስራዎች ሙቀተን በጠበቀ መልኩ ማስቀጠል የሚያስፈልግበት ነው” አሉ የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለፁ።

ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በዛሬው እለት ባስተላለፉት መልእክት፥ ያለንበት ወቅት የህዝቡን ኑሮ የሚለውጡ እና የብልፅግና ግቦችን በተያዘው ጊዜ ውስጥ ለማሳካት የሚረዱ የልማት ስራዎችን ያለእረፍት መስራትን የሚጠይቅ ነው ብለዋል።

“በምኞት ሳይሆን ሰርተን በእርዳታ እና በግዢ ከውጭ የሚገባን የስንዴ እናስቆማለን፤ ጠባቂነትን ታሪክ እናደርጋለን” ብለን ይህንን የበጀት ዓመት ስራ ጀምረናልም ብለዋል አቶ ሽመልስ።

ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በፈረቃ በማምረት ምርታማነትን ለማሳገድ ከተጀመረው ጥረት ጎን ለጎን በመስኖ ልማት ላይ ትኩረት በማድረግ ለገበያ የሚሆን ምርት እየተመረተ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ባለፈው ዓመት በተሰራው ስራም ከውጭ ይገባ የነበረን የቢራ ገብስ በሀገር ውስጥ መተካት መቻሉንም ነው ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ያስታወቁት።

በተያዘው ዓመት ደግሞ ከውጭ የሚገባ የስንዴ ምርትን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ተጨባጭ ስራ መጀመሩንም ገልፀዋል።

ለዚህም የክልሉ አመራሮች በተወሰኑ ዞኖች ባደረጉት የመስክ ጉብኝት እና ክትትል ለመስኖ ልማት በአስፈላጊው መንገድ መሬት ዝግጅት ስራ እየተከናወነ መሆኑን መመልከት ችለዋልም ብለዋል።

በተጨማሪም የመስኖ ልማት ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች አቅርቦትም በተቻለ አቅም እየተሟላ መሆኑን በመጥቀስ፤ ለዚህም አርሶ አደሮች፣ የግብርና ባለሙያዎች እና በሁሉም ደረጃ የሚገኝ የመንግስት መዋቅር በምርት ራስን መቻልንና የቤተሰብን የምገብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ቀሪውን ለገበያ ለማቅረብ ያለ እረፍት መስራት ይጠበቅባቸዋልም ብለዋል።

“አንቅፋቶች ቦታ ባለመስጠት ዘንድሮ የተያዘውን እቅድ ከግብ በማድረስ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ መደገፍ ይጠበቅብናልም” ብለዋል አቶ ሽመልስ በመልእክታቸው።

በዚህ እድል በመጠቀምም በማሳ ላይ ያሉ የደረሱ ሰብሎችን ያለ ምንም ብክለት መሰብሰብ እንደሚገባም አስታስወሰዋል።

አቶ ሽመልስ በምልእክታቸው፥ ሌላው ሙሉ ትኩረት የሚሰጠው ስራ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ መሆኑንም አነስተዋል።

ባለፈው ዓመት “ የማንጨርሰውን አንጀምርም፤ የጀመርነውን እንጨርሳለን” በሚል መሪቃል ወደ ስራ በመግባት በርካታ የልማት ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸውን እና ከዚህም ልምድ ማግኘት መቻሉን ጠቅሰዋል።

ከባለፈው ዓመት የፕሮጀክት አፈፃፀም ልምድ በመቅሰም በተያዘው ዓመትም የህዝቡን ኑሩ የሚቀይሩ የልማት ፕሮጀክቶችን ለመስራት መታቀዱን በመግለፅ፤ ከእነዚህም ውስጥ የትምህርት ተቋማት እንዲሁም መንገድ፣ ንፁህ የመጠጥ ውሃ፣ የጤና ተቋማት እና ሌሎችን መሰረተ ልማቶች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

“እነዚህን የልማት ፕሮጀክቶች ሙሉ ትኩረት በመስጠት እና በሙሉ አቅም በመስራት አስመርቀን መጠቀም ይጠበቅብናልም” ብለዋል።

በክልሉ የተጀመረው የዜግነት አገልግሎት በርካታ ኢኮኖሚያዊ እና የስነ ልቦና ጥቅሞችን እያስገኘ መሆኑን የገለፁት አቶ ሽመልስ፥ ምሁራን እና በክልሉ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ባላቸው አቅም በሙሉ በትውልድ ግንባታ ላይ በተጀመረው የዜግነት አገልግሎት ላይ እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል።

ርእስ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አክለውም፥ “የህግ የበላይነትን እና የሀገርን ህልውና ለማስጠበቅ የተጀረው ዘመቻ በድል ለማጠናቀቅ ዋዜማው ላይ ደርሰናል” ብለዋል።

“ስለዚህም ባለን አቅም በሙሉ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጋር በመሆን፤ በስራዎች ላይ በመሳተፍ ለድል እንስራ” ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

በከፍተኛ ተሳትፎ በክልሉ የተጀመረው የህግ የበላይነትን የማስከበር እና አስተማማኝ ሰላምን የማረጋገጥ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.