Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ እና የሳሲጋ ወረዳ ነዋሪዎች ለሃገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 18፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ እና በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ወለጋ ዞን የሳሲጋ ወረዳና የአከባቢው ነዋሪዎች ለሃገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ አድርገዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ህግን ለማስከበር ራሱን መስዋእት አድርጎ በግንባር እየተፋለመ ለሚገኘው የሃገር መከላከያ ሰራዊት የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች ፣ነጋዴዎችና ባለሃብቶች ከ69 ሚሊየን ብር በላይና በአይነት ደግሞ ከ 8 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አድርገዋል።
በዚህ ወቅት የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ሃላፊ አቶ መለስ አለሙ እንዳሉት ህብረተሰቡ ከሃዲው የህወሓት የጥፋት ቡድን በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት እና በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈጸመው እኩይ ተግባርን ከማውገዝ ባለፈ ከመከላከያ ሰራዊት ጎን እንደሆነ እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት የሚመሰገን ነው ብለዋል።
የሃብት ድጋፉን የተረከቡት የመከላከያ ሴቶች ጉዳይ ዳይሬክተር ሜጀር ጄንራል ጥሩዬ አሰፌ በበኩላቸው ህዝቡ ለመከላከያ ሰራዊት እያሳየ ያለው ድጋፍ እና የሚሰጠው ሞራል ሰራዊቱን ለበለጠ ስራ እና መስዋእትነት የሚያነሳሳ ነው ብለዋል።
በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ወለጋ ዞን የሳሲጋ ወረዳና የአከባቢው ነዋሪዎች ለሃገር መከላከያ ሰራዊት 27 የእርድ ሰንጋዎችን ድጋፍ አድርገዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም 38 የአከባቢው ሚሊዎች የመከላከያ ሰራዊቱን መቀላቀላቸው ታውቋል፡፡
በዚህ ወቅት የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ደረጄ ደርባባ እንዳሉት በሃገር መከላከያ ሰራዊት በሰሜን እዝ አባላት ላይ የተፈፀመው የከሃዲነት ጥቃት በእጅጉ ሚያሳዝን እና አሳፋሪ ተግባር ነው ብለዋል፡፡
ሰራዊቱ አሁን ጀመረው ህግ የማስከበር ስራ በድል እስኪያስፈፅም የሳሲጋ ወረዳና የአከባቢው ነዋሪዎች ከመከላከያ ሰራዊቱ ጎን እንደሚሆኑ አስታውቀዋል፡፡
በሌላ በኩል አንድ ግለሰብ ለጦር ሀይሎች ኮምፕሪሄንሲቭ ሆስፒታል 228 ሺህ ብር የሚያወጣና የኮቪድ19ኝን ለመከላከል የሚረዳ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል፡፡
ድጋፉን ያስረከቡት የአዲስ መንገድ ጀነራል ትሬዲንግ ተወካይ አቶ ሀብቶም መረሳ፥ ድጋፉን እንደ ሀገር ኮቪድ 19ኝን የመከላከል ጥረት ውስጥ የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት በማሰብ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም ለአካባቢ ፅዳት የሚያግዙ ቁሳቁሶችን እንደሚለግሱ ቃል ገብተዋል ።
የሆስፒታሉ አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ሀይሉ እንደሻው በበኩላቸው፥ እየተደረገ ካለው ህግን የማስከበር ዘመቻ ጎን ለጎን ኮቪድ 19 ሰውን እንዳይጎዳ በሆስፒታሉ የሚሰጡ አገልግሎቶች የተሻሉ እንዲሆኑ ድጋፉ እንደሚያግዝ መናገራቸውን መከላከያ ሰራዊት አስታውቋል።

በመከላከያ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና የሆስፒታሉ ፈጣን ምላሽ ሰጪ ቡድን አስተባባሪ መ/አ ዶ/ር ተክለማሪያም ዱጉማ ፣ እንደዚህ ዓይነት ድጋፍ ታካሚዎችን ለማገልገልና ሀገሪቱን ለማሳደግ ትልቅ ሚና ስላለው ሌሎች ግለሰቦችና ድርጅቶች ከሆስፒታሉ ጎን እንዲቆሙ ጠይቀዋል ።

በሃይማኖት ኢያሱ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.