Fana: At a Speed of Life!

የህወሃት ጁንታ አስቦት የነበረው ሀገር የማፍረስ ህልም ከሽፏል- የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 20 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የህወሃት ጁንታ አስቦት የነበረው ሀገር የማፍረስ ህልም መክሸፉን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ገለጸ።

የህወሓት ጁንታ ለመቆጣጠር እስካሁን በተመዘገበው ድልም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፏል።
ከሌሎች የመረጃና ፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የጁንታውን ድብቅ ሴራ በማጋለጥ ለህግ ለማቅረብ በሚደረገው ጥረትም ኃላፊነቱን ለመወጣት እየሰራ መሆኑን በመግለጫው አመልክቷል።

በስግብግቡ የጁንታ ላይ የተገኘው አኩሪ ድል የመላው የአገራችን ህዝቦች በተለይም ደግሞ የትግራይ ህዝብ አኩሪ የትግል ውጤት በመሆኑ ተቋሙ የተሰማውን ደስታ ገልጿል።

የህወሓት ስግብግብ ጁንታ በፖለቲካው አውድ የደረሰበትን ሽንፈት ተከትሎ ትግራይ ክልል በመመሸግ ህገወጥ ተግባራትን ሲፈፅም ቆይቷልም ብሏል የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በመግለጫው።

ጁንታው የሰሜን ዕዝ የሰራዊቱ አባላትና የፌዴራል ፖሊስ አባላት ላይ ጥቃት በመፈጸም እንዲሁም በአማራ ክልል ህዝቦች ላይ ግልፅ ጦርነት በማወጅ የአገርን ብሄራዊ ደህንነትና ጥቅም በሚጻረር ከፍተኛ ክህደት መፈፀሙንም በመግለጫው አመልክቷል።

ቡድኑ ጦርነቱን የጀመረው በግልፅ፣ በተደራጀ እና በከዳተኛ አባሎቹ ጭምር ተገቢ ጥናት ፈፅሞ የሰራዊቱን ቁልፍ ትጥቆች፣ ስንቆች፣ የማዘዣ ጣቢያዎችና የዕዝ ሰንሰለቶች ለመቆጣጠርና ለመበጣጠስም በማለም መሆኑን ጠቅሷል።

ይሁን እንጂ ህልሙ ሙሉ በሙሉ ባሰበው ልክ አልተሳካለትም፣ ከሽፏል፣ ያሳካው ነገር ቢኖር ትውልድ ይቅር የማይለው አሳፋሪ እና አስነዋሪ ታሪክ ማስመዝገብ ነው ብሏል።

የስግብግብ ጁንታ ህልም እንዳይሳካ በራሱ የግንኙነት ኔትወርክ ውስጥ ሰርጎ በመግባት፣ ተባባሪ አካላትና አባላትን፣ የወገንን ኃይል እንዲሁም ሰላም ወዳዱን የትግራይ ህዝብ በመጠቀም መረጃ በመሰብሰብና በመተንተን ለተመዘገበው ድል ድጋፍ ማድረጉንም አስታውቋል።

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከሌሎች የመረጃና የፀጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት የጁንታው ድብቅ ሴራ እንዳይሳካ ማክሸፉንም ገልጿል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.