Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ያለባትን የብድር ጫና ለመቀነስ የንግድ ሚዛን መዛባትንና የሀገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብን ማሳደግ እንደሚገባት  ምሁራን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 21፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ)ኢትዮጵያ ያለባትን የብድር ጫና ለመቀነስ የንግድ ሚዛን መዛባትንና የሀገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብን ማሳደግ እንደሚገባ የዘርፉ ምሁራን ገልጸዋል።

የአለምአቀፉ የገንዘብ ተቋም አይ ኤም ኤፍ አፍሪካ ላይ ትኩረቱን አደርጎ ለመጨረሻ ጊዜ ባወጣው ሪፖርት ባለፉት 3 አመታት የኢትዮጵያ ዓመታዊ ኢኮኖሚያዊ እድገት መቀዛቀዝ ቢታይበትም ከሰሀራ በታች እና ከአለም አማካይ የእድገት ምጣኔ አኳያ ግን አሁንም ከፍተኛ ከሚባሉት ተርታ መመደብ የሚችል መሆኑን ጠቁሟል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው ምሁራን በበኩላቸው፥ አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይ ኤም ኤፍ ለሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ የሰጠው የ2 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ችግሮቹን ለመቅረፍ የሚውል መሆኑ በመልካም ጎን የሚነሳ መሆኑን አንስተዋል።

የተመዘገበው ዕድገት ምንም እንኳን እንደሚባለው ፈጣን እና ከፍተኛ ቢሆንም እድገቱ የተመዘገበው የሀገሪቱ አምራችነትና ምርታማነት አድጎ ሳይሆን፣ የመንግሥት ወጪ በመጨመሩ የመጣ እንደሆነ ምሁራን ይስማማሉ።

ለዚህ ደግሞ በሀገሪቱ የሚታየውን ሰፊ የግንባታ መጠን ለአብነት ይጠቅሳሉ።

በመንግስት የተሰሩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እና የተለያዩ ፕሮጀክቶች ዋነኛ ወጪያቸው ብድርን መሰረት ማድረጉ ደግሞ በምጣኔ ሃብቱ ላይ አሁን ለሚታየው የውጭ እዳ ጫና ተጽእኖ ምክንያት መሆኑ ይነሳል።

ከዚህ ሀሳብ ጋር የሚስማሙት የብሄራዊ ባንክ አማካሪ አቶ መለሰ ምናለ ባለፉት አመታት የተስተናገደው መንግስት ተኮር የኢንቨስትመንት ስራዎች መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት እድገትንም ለማስመዝገብ አጋዥ ቢሆኑም  በሀገሪቱ የብድር ጫና እንዲጨምር የነበረው አስተዋጽኦ ግን ከፍተኛ ነው ይላሉ።

የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ሪፖርት ኢትዮጵያን ከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ ከገቡ ሀገሮች ተርታ መድቧታል።

የውጨ እዳ ጫና ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) አኳያ እ.ኤ.አ. ከ2016 ጀምሮ ከ55 በመቶ በላይ ድርሻውን ይዞ መቆየቱንና በመጪውም ዓመት በተመሳሳይ አሃዝ ሊቀጠል እንደሚችል ትንበያውን አስቀምጧል።

በአዲስ አበባ  ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ባለሙያ እና መምህር ዶክተር አጥላው አለሙ፥ ከዚህ ቀደም አዋጪነታቸው ሳይጣራ መንግስት በብድር የጀመራቸው የተለያዩ የልማት ድርጅቶች አትራፊ እና ውጤታማ አለመሆናቸው ከብድር ጫና እስከ ውጨ ምንዛሬ እጥረት የራሳቸውን አሻራ አኑረዋል ባይ ናቸው።

እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በርካታ ፍጆታዎችን ከውጭ ሀገር በማስገባት ምጣኔ ሀብቱን የሚደግፋ ሀገራት ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሬ ተቀማጭ እንዲኖረው ኢኮኖሚው ይጠይቃል።

ይህ ደግሞ የውጪ እዳን ለመክፈል ከሚፈለገው ምንዛሬ ጫና ጋር ሲታከል ምጣኔ ሃብቱ በሚጠበቀው መጠን እንዳይጓዝ ምክንያት ሆኗል።

የእነዚህ ሁነቶች ተያያዠነት ሀገሪቱ አሁን ለምትገኝበት የኢኮኖሚ መንገጫገጭ መሰረቶች ሆነዋል የሚሉት ዶክተር አጥላው፥የዋጋ ንረት የውጭ ምንዛሬ እና ሌሎችም ከዚሁ ጋር የሚያያዙ መሆናቸውን ያነሳሉ።

መንግስት አሁንም ወደ ሀገሪቱ በተለያየ መንገድ የሚገቡ የውጭ ገንዘቦችን አዋዋል በጥብቅ ከመቆጣጠር አንስቶ በዘላቂነት  የግል ዘርፉን ማበረታት፣ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትን በሰፊው መሳብ እንዲሁም በመንግስት በሚሰሩ ፕሮጀክቶች አዋጭነት ላይ ትኩረት ያሸዋል ብለዋል።

አይኤም ኤፍ በቅረቡ ኢትዮጵያ እያከናወነች ለሚገኘው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የሚውል የ2 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ማድረጉ ይታወቃል።

ይህ የገንዘብ ድጋፍ በረጅም ጊዜ በኢኮኖሚው ላይ የሚደረጉ ማሻሻያዎችን ገቢራዊ ለማድረግ እንደሚያግዝ ይጠበቃል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሞያው ዶክተር ሲሳይ ረጋሳ፥ይህ ብድር እንደከዚህ ቀደሙ የመንግስት የግንባታ ፕሮጀክቶችን ለማስፈጸም ሳይሆን የንግድ ሚዛን መዛባትነ ለማረቅ፣ የውጭ ምንዛሬ ችግሮችን ለመቅረፍ፣ የብድር ጫና ተጋላጭነትን ለመቀነስና የመንግስት የገቢ አሰባሰብ ስርዓትን ለማሳደግ የሚውል መሆኑ መልካም ውጤት ሊያመጣ ይችላል ብለዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር እዮብ ተካልኝ በበኩላቸው፥ በከፍተኛ የውጪ ብድር የተሰሩ የመንግስት የልማት ተቋማት የነበረባቸው ችግር ተለይቶ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው በተለይ ከከፍተኛ ብድር ጋር ተያይዞ ስማቸው ሲጠራ የነበሩ የመንግስት የልማት ድርጀቶችን ከማስተካከል ጀምሮ መንግስት የሚሳተፍባቸው የልማት ፕሮጀክቶች የተመረጡ እንዲሆኑ እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የብሄራዊ ባንክ አማካሪው አቶ መለሰ ደግሞ የውጭ እዳ ጫናን ለመቀነስ የውጭ ምንዛሬ ማግኛ መንገዶችን ማስፋት እና ለገቢ እቃዎች እና ሌሎች አገልግሎቶች የሚወጡ ወጪዎችን በዛ ለመሸፈን መንቀሳቀስ ያስፈልጋል ባይ ናቸው።

ይህን ለማድረግም በውጨ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥ የውጭ ሀገራት ገንዘቦችን እንዲቆጥቡ ወለድ እና ሌሎች አሰራሮችን ማጠናከር ያስፈልጋል   ነው ያሉት ።

 

 

በዳዊት በሪሁን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.