Fana: At a Speed of Life!

የምርት ገበያ ባለሥልጣን አሠራር ሊፈተሽ ይገባል – የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች

አዲስ አበባ፣ ህዳር 28፣ 2013 (ኤፍቢሲ) የሀገሪቱን የውጭ ንግድ ለማስፋት ከምርት ገበያ ባለሥልጣን ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ የክልል ርዕሳነ-መስተዳድሮች ጠየቁ።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከክልል ርዕሰ መስተዳድሮችና የዘርፉ ተወካዮች ጋር በውጭ ንግድ ችግሮችና መፍትሄዎች ላይ ያተኮረ ውይይት ዛሬ አድርጓል።

በውይይቱ ርዕሰ መስተዳድሮቹ በየክልሎቻቸው የሚስተዋሉ ችግሮችን በማውጣት ዘርፉን ማጠናከር ይችላሉ ያሏቸውን የመፍትሄ ሐሳቦች አቅርበዋል።

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው የውጭ ንግድን ለማጠናከር ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በጥራትና በብዛት ማሻሻል ይገባል ብለዋል።

ትናንሽ የእርሻ መሬት ያላቸው አርሶ አደሮችን ሊጠቅሙ የሚችሉ በውጭ ንግድ የተሰማሩ ባለሃብቶችን በስፋት የመሳብ ሥራ ሊጠናከር እንደሚገባ አንስተዋል።

የሚመሩት ክልል እስካሁን የጀመራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው የፌደራል መንግሥቱም ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

በተለይም ደግሞ ከምርት ገበያ ባለሥልጣን ጋር የሚነሱትን ቅሬታዎች በቅጡ በማጤን ለችግሩ ሁነኛ መፍትሄ ማፈላለግ ይገባል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው፣ የውጭ ንግድ ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ የብድር አቅርቦት መስፋት ያስፈልጋል ብለዋል።

በግንባታ ላይ ያሉትን የደረቅ ወደብ አገልግሎቶች በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረግ አላስፈላጊ ወጪን መቀነስና አሰራርን ማሳለጥ እንደሚገባም አንስተዋል።

ወደ ጎረቤት ሀገራት በሕገ-ወጥ መልኩ የሚወጡትን የእንስሳት ሃብት ለመቆጣጠር ሕጋዊ የግብይት ሥርዓት ሊጠናከር እንደሚገባ ነው ያስረዱት።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ እንዳሉትም የንግድ ሥርዓቱ አምራቹንና አርብቶ አደሩን ከግምት ያስገባ ሊሆን ይገባዋል።

በክልሉ የምርት አቅርቦትን በጥራት ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በፌደራል በኩል የውጭ ንግድ የተመለከቱ የሕግ ማዕቀፎች ሊታዩ ይገባልም ነው ያሉት።

በተለይም የንግድ ፈቃድ አወጣጥ ሥርዓት ዳግም ሊታይ እንደሚገባው አውስተዋል።

ዘርፉ በውድድር የተሞላ እንዲሆን ማድረግ፣ የብድር አቅርቦት ማስፋትና፣ ለውጭ ንግድ አስፈላጊ የሆኑ የሎጂስቲክ አቅርቦት መሟላት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

የኅብረት ሥራዎች አደረጃጀትና አስተዳደራቸው እንዲሁም የሚቀርብላቸው የፋይናንስ ድጋፍ በተመለከተ የሚደነግጉ ሕጎች ላይ መሻሻል እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በበኩላቸው፣ የውጭ ንግድ ሥራን ለማጠናከር የተለያዩ አዎንታዊ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ተናግረዋል።

በተለይም ከብድር አቅርቦት ጋር በተያያዘ ሚኒስቴሩ አቅርቦቱን በስፋት እያመቻቸ እንደሆነና ነገር ግን ብድሩን በአግባቡ በመጠቀም ረገድ ክፍተት መኖሩን ጠቅሰዋል።

ከመሰረተ ልማት ጋር በተያያዘ ችግሮችን ለመፍታት በርካታ ጥረቶች መደረጋቸውን ገልጸው፤ ከምርት ገበያም ጋር ተያይዞ የሚነሱት ችግሮች የዘርፉ ተዋናዮች በመብዛታቸው መሆኑንም ጠቁመዋል።

ያም ሆኖ በክልል ርዕሳነ-መስተዳድሮቹ የተነሱትን ሐሳቦች በግብዓትነት እንደሚወስዱትም አስታውቀዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አማካሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ የክልል አስተዳደሮች አሁን ላይ ለውጭ ንግድ ያሏቸውን አቅም ማወቅና መለየት አለባቸው ሲሉ አንስተዋል።

ጎን ለጎንም በውጭ ንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች በተሰማሩባቸው ዘርፎች ላይ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በዝርዝር መለየትና መፍትሄም መሰንዘር እንደሚገባም ነው ያነሱት።

ክልሎቹ በዚሁ ጉዳይ ላይ ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር በቅርቡ ውይይት እንዲያደርጉና ለችግሮቹ መፍትሄም እንዲያቀርቡ አምባሳደር ግርማ ብሩ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.