Fana: At a Speed of Life!

የመንግስት ቀዳሚ ስራ የመሰረተ ልማት አውታሮችን መልሶ የመጠገንና የተጎዱ ዜጎችን ማቋቋም ነው- አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን

አዲስ አበባ፣ ህዳር 29፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በትግራይ ክልል የመሰረተ ልማት አውታሮችን መልሶ የመጠገንና የተጎዱ ዜጎችን መልሶ ማቋቋም የመንግስት ቀዳሚ ተግባር መሆኑን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ፍሰት ቃል አቀባይ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለፁ።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ፍሰት ቃል አቀባይ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ስለ ትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ በተለይም በክልሉ ስላለው የሰብዓዊ ዕርዳታ እንቅስቃሴ መግለጫ ሰጥተዋል።

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በመግለጫው፥ የህግ ማስከበር ዘመቻው “ወንጀለኞችን የማደንና የመልሶ ግንባታ ምእራፍ” መድረሱን ገልፀው፤ በዚህ ምዕራፍ መንግስት የመሰረተ ልማት አውታሮችን መልሶ የመጠገን እና በግጭቱ የተጎዱ ዜጎችን መልሶ ማቋቋም ቀዳሚ ስራው መሆኑን አስረድተዋል።

የህወሓት ወንጀለኞች መደበቂያ ስፍራ አስቀድሞ የተገኘ ሲሆን፥ ወንጀለኞችን የመያዙ ስራ ተጠናቆ በቅርቡ ይፋ እንደሚሆንም አምባሳደሩ አክለው ገልጸዋል።

አንዳንድ የእርዳታ ድርጅቶች እና የመገናኛ ብዙሃን ወደ ክልሉ በቀላሉ ለመድረስ ባለመቻላቸው የሚያሰሙት ቅሬታ መኖሩን ጠቁመው፤ ሆኖም የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ ተቋማትን ጨምሮ በክልሉ ስለሚከናወኑ የአሠራር ሕጎች ከፌደራል መንግሥት ከሚሰጡት አቅጣጫዎች ጋር መጣጣም እንደሚኖርባቸው አንስተዋል።

ይህም የሚሆነው ለሃገሪቱ ሉዓላዊነት መከበር ብቻ ሳይሆን ለራሳቸው ደህንነት ነውም ብለዋል አምባሳደር ሬድዋን።

የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ በበኩላቸው÷ በመንግስታዊ እና መንግታዊ ባልሆኑ የእርዳታ ድርጅቶች መካከል ማስተባበር ስልቶች ላይ ትኩረት በማድረግ በክልሉ እየተከናወነ ስላለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ገለፃ አድርገዋል።

የመንግስት ድርጅቶች እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የድጋፍ የሚያስተባብሩ ወደ 10 የሚጠጉ ክላስተር በማቋቋም የሰብዓዊ ዕርዳታ ፕሮጀክቱን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ክላስተሮቹም በግብርና እና እንስሳት፣ በውሃና ሳኒቴሽን፣ በጤና፣ በምግብ እና ምግብ ነክ ባልሆኑ ቁሳቁሶች፣ በሎጂስቲክስ፣ በሴቶች እና በልጆች በውስጣቸው ያካተቱ መሆናቸውንም ነው የጠቆሙት።

የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚጀምረው በትግራይ የሕግ ማስከበር ሥራ ከመጀመሩ በፊት ቀደም ሲል ተጋላጭ በሆኑት ተረጂዎች መሆኑንም አመላክተዋል።

ሆኖም በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች የሚገኙና ሰብዓዊ ድጋፍ የሚፈልጉ ዜጎችን ለመለየት ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

 
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
 
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
 
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
 
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
 
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
 
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.