Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያን በከፍተኛ የእድገት መንገድ እንድትጓዝ የሚያስችላት የ10 ዓመት ብሔራዊ ዕቅድ ጸድቋል – ጠ/ሚ ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 2፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት ኢትዮጵያ በከፍተኛ የእድገት መንገድ እንድትጓዝ የሚያስችላትን የ10 ዓመት ብሄራዊ የልማት ዕቅድ አፀደቀ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ  ኢትዮጵያን ወደ ዕድገት ማማ በማስፈንጠር አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት እንድትሆን የሚያስችላት የኢትዮጵያ የዐሥር ዓመት ብሔራዊ ዕቅድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አፅድቋል ብለዋል።

ዕቅዱ በተለይም በሰላም ግንባታ እና ተቋማዊ ሕዳሴ ላይ የሚያተኩሩ ዐሥር ምሦሦዎች አሉት ነው ያሉት።

ይህ የልማት ዕቅድ ከሕዝቡ ጋር ሰፊ ምክክር ተደርጎበት የዳበረና መግባባት ተደርሶበት የዜጎች ባለቤትነት የተረጋገጠበት ዕቅድ ሲሆን፣ ሂደቱም ከታች ወደ ላይ እና ከላይ ወደ ታች በሆነ የዕቅድ አዘገጃጀት መንገድን ተከትሎ በዘርፎች ውስጥና በዘርፎች መካከል ትስስር እንዲኖር በማድረግ የተሰናዳ ነው ተብሏል፡፡

የአስር ዓመት የልማት ዕቅዱ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ገበያ-መር የኢኮኖሚ ሥርዓት በመከተል የግል ዘርፉን ጉልህ ሚናና ተሳትፎ በማሳደግ የበለጸገች ሀገር መገንባት፤ የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታን በመፍጠር ፈጣንና ዘላቂነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብና ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚያስችል ተጠቁሟል።

አጠቃላይ የኢኮኖሚ ምርታማነት፣ ጥራትንና ተወዳዳሪነትን በማጐልበት የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ማረጋገጥ፣ የማኅበራዊና የመሠረተ ልማት ጥራትንና ተደራሽነትን በማረጋገጥ ዜጎች የልማቱ ባለቤትና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ እና ሰላምና ፍትሕ የሚያረጋግጡ ጠንካራ ሥርዓት በመገንባትና የሕግ የበላይነትንና ሰብዓዊ መብትን በማስከበር የዜጎችን ደኅንነት ማረጋገጥ የሚሉ ዋና ዋና ዓላማዎች እንዳሉት ከፕላን እና ልማት ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የልማት ዕቅዱ ጥራት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት እና የጋራ ብልጽግናን፣ የኢኮኖሚ ምርታማነት እና ተወዳዳሪነትን፣ ዘላቂ የዕድገት እና የልማት ፋይናንስን፣ የግሉን ዘርፍ የኢኮኖሚ ዕድገት መሪነት፣ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎችን የሚቋቋም አረንጓዴ ኢኮኖሚ በመገንባት የሥርዓት ለውጥ እና የልማት ተጠቃሚነት እና ማኅበራዊ አካታችነትን ለማረጋገጥና የፍትሕ ተደራሽነት እና ውጤታማ መልካም አስተዳደርን ማስፈን እንዲሁም ዘላቂ የሰላም ግንባታና ጠንካራ ቀጠናዊ ኢኮኖሚያዊ ትብብርን ማረጋገጥ ቁልፍ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ አተኩሮ የሚሠራ እንደሆነ ተነግሯል፡፡

በተጨማሪም፣  የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኅትመት እና የብሮድካስት መገናኛ ብዙኃን መተዳደሪያ  ሆኖ የሚያገለግለውን እና ለማኅበራዊ ሚዲያ የሕግ ማሕቀፍ ሆኖ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚተገበረውን፣ ረቂቅ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ዐዋጅ አጽድቋል። የዘርፉን ግዴታዎች እና ኃላፊነቶች የሚተነትነው ዐዋጅ፣ የመረጃ እና የፕሬስ ነጻነት ተግባራዊነትን በከፍተኛ ሁኔታ የሚደግፍ ነው።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.