Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካ የፋይዘር እና ባዮኤንቴክ ክትባት ለአስቸኳይ አገልግሎት እንዲውል ፈቀደች

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 3፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ የፋይዘር እና ባዮኤንቴክ ክትባት ለአስቸኳይ አገልግሎት እንዲውል መፍቀዷ ተሰምቷል፡፡

የአሜሪካ የምግብ እና የመድኃኒት አስተዳደር የፋይዘር እና የባዮኤንቴክ ክትባት ለአስቸኳይ አገልግሎት እንዲውል መፍቀዱ ተነግሯል፡፡

በአሜሪካ ከ295 ሺህ በላይ ሰዎችን ህይወት ያሳጣውን ወረርሽኝ ለመከላከል ጉልህ ምዕራፍ ነው ሲልም ገልጾታል፡፡

ክትባቱ የኮቪድ-19 በሽታን 95 በመቶ እንደሚከላከል የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

እስካሁን በብሪታኒያ ፣ ካናዳ ፣ ባህሬን እና ሳውዲ አረቢያ ክትባቱ ጥቅም ላይ እንዲውል ፍቃድ ተሰጥቷል፡፡

እንደነዚህ ሀገራት ሁሉ አሜሪካ የመጀመሪያ ክትባቱን ለአረጋውያን ፣ ለጤና ሰራተኞች እና ለድንገተኛ ሠራተኞች የምትሰጥ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በአሜሪካ ከህዳር ወዲህ በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ለህልፈት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱ የሚታወቅ ነው፡፡

በአለም አቀፍ ደረጃ እስካሁን ከ71 ሚሊየን 438 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ ከ1ነጥብ 6ሚሊየን በላይ ሰዎች ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡

ምንጭ፡- ቢቢሲ እና ዎርልድ ኦ ሜትር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.