Fana: At a Speed of Life!

በሦስት ሳምንታት ውስጥ 1.8 ቢሊዮን ብር ግምት ያለው ድጋፍ ለመከላከያ ተሰብስቧል – ሰላም ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 3፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሦስት ሳምንታት ውስጥ ለአገር መከላከያ ሰራዊት 1.8 ቢሊዮን ብር ግምት ያለው ድጋፍ ከህዝብና ከተለያዩ ተቋማት መሰብሰቡን የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ።
በችግሩ ጉዳት ለደረሰባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚሆን አስፈላጊው ሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ሚኒስትሯ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ከሁሉም የአገሪቱ ማህበረሰብና በውጭ ከሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለአገር መከላከያ ሰራዊት በጥሬ ገንዘብና በቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል።
በጥሬ ገንዘብ በባንክ በማስገባት እና በመሰል መንገዶች ከዚህ ውስጥም 1.5 ቢሊዮን ብር ተሰብስቧል።
በኢትዮ-ቴሌኮም በኩል በተከፈተ የሞባይል መልዕክት ገንዘብ ማሰባሰቢያ 2.6 ሚሊዮን ብር በሚደርስ ድጋፍ ከ84 ሺህ የሚበልጡ ዜጎች መሳተፋቸውን ገልጸዋል።
በሀብት ማሰባሰቡ ሂደት ግለሰቦች፣ የመንግሥትና የግል ተቋማት እና በውጭ ያሉ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለሃገራቸውና ለመከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ፍቅርና አክብሮት ለመግለፅ ተሳትፈውበታል ብለዋል።
መንግሥት እየወሰደ ባለው የህግ ማስከበር ስራ ላይ የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የአማራ እና የአፋር ልዩ ኃይሎች እና ሌሎች የጸጥታ አካላት የሰሩትን የሀገር ማዳን ስራ ዜጎች በከፍተኛ አክብሮት እየደገፉት መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የህዝቡ አስተዋጽኦ በገንዘብና በሌሎች ሃብቶች ብቻ የሚወሰን እንዳልሆነ የገለጹት ወይዘሮ ሙፈሪያት፤ “ለአገር መከላከያ ሰራዊትና በሀገር ማዳን ተልዕኮው ላይ አስተዋፅኦ ላደረጉ የፀጥታ አካላት ያለውን ልባዊ ክብርና ፍቅር የገለፀበት ነውም”ብለዋል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.