Fana: At a Speed of Life!

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ በኢትዮጵያ የኳታር አምባሳደር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 7፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ በኢትዮጵያ የኳታር አምባሳደር ሐመድ አል ዶሳሪ ጋር ተወያዩ፡፡

በውይይታቸውም በኢትዮጵያና በኳታር መካከል ረዥም ጊዜ የቆየ የኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላቸው አፈ ጉባኤው ገልፀዋል።

አቶ አደም ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ለአምባሳደሩ ገለፃ ያደረጉ ሲሆን የሁለትዮሽ ግንኙነትና ትብብሩ በይበልጥ በሚጠናከርበት ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

በዚህም አፈ ጉባኤው የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል ባካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻን እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግስቱ ከተሰጡት ስልጣንና ተግባር መካከል ሕገ መንግስቱን መተርጎም አንዱ መሆኑን ገልጸው ስድስተኛው ሀገር አቀፍና ክልላዊ ምርጫን በተመለከተ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ከሕገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ በቀረበለት የውሳኔ ሀሳብ መሰረት እንዲራዘም መወሰኑን አስረድተዋል፡፡

ውሳኔውን ተከትሎ ከትግራይ ክልል በስተቀር ሁሉም ክልሎች የፌዴሬሽን ምክር ቤት የወሰነውን ሕገ መንግስታዊ ውሳኔ አክብረው ተፈጻሚ ማድረጋቸውን አፈ ጉባኤው ተናግረዋል።

ነገር ግን የህወሓት አመራሮች ሕገ መንግስቱንና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን በሚጻረር መንገድ የክልል የምርጫ ኮሚሽን በማቋቋም ህገ ወጥ ምርጫ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡

ሆኖም የፌደራል መንግስት ሊወስዳቸው የሚችላቸው ሕገ መንግስታዊ እርምጃዎችን ለትግራይ ሕዝብ ሲል በማዘግየት ለህገወጡ የሕወሓት ቡድን በቂ ጊዜ መስጠቱን አፈ-ጉባኤው ጠቅሰዋል፡፡

ይሁንና ሕገ ወጡ የህወሓት ጁንታ ቡድን በሰሜን ዕዝ በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ እጅግ አስነዋሪ ጥቃትና የሀገር ክህደት መፈጸሙን ተከትሎ የፌደራል መንግስት ተገዶ ወደ ሕግ ማስከበሩ ዘመቻ መግባቱን አፈ-ጉባኤው ማስረዳታቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ዘመቻው በድል ተጠናቆ ወንጀለኞችን የማደንና የተፈናቀሉ ዜጎችንና የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ የማቋቋምና የመገንባት ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

በሰላም ሚኒስቴር አስተባባሪነት ዜጎችን መልሶ የማቋቋምና ሰብዓዊ ድጋፎችን የማቅረብ ሥራን የሚሰራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሕዝብን በማስተባበር ስራ መጀመሩን አብራርተዋል፡፡

አምባሳደር ሐመድ አል ዶሳሪ በበኩላቸው በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ እጅግ የሚበረታታ መሆኑን ገልፀው ለስኬታማነቱ የኳታር መንግስት የልማት ድጋፍና ትብብር እንደማይለየው አብራርተዋል።

የኳታር ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል አምባሳደሩ፡፡

ኳታር በፈረንጆቹ 2021 ጥቅምት ወር ላይ የሹራ ምክር ቤት ምርጫ እንደምታካሂድ ጠቅሰው በዚህም የህዝቡ ዴሞክራሴያዊ ተሳትፎ እንደሚጨምር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.