Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል በ10 ቢሊየን ብር እየተገነቡ ያሉ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች በዚህ አመት ማምረት ይጀምራሉ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 7፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በ10 ቢሊየን ብር እየተገነቡ ያሉ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች በዚህ አመት ማምረት እንደሚጀምሩ የክልሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

ኮርፖሬሽኑ የቡልቡላ የተቀናጀ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ፓርክን ጨምሮ ሌሎች የግብዓት አቅራቢ ኢንዱስትሪዎችን ለባለሃብቶች፣ ለማህበራትና ለኢንቨስትመንት ተቋማት የማስተዋወቅ ዓላማ ያለው መድረክ በአዳማ ከተማ አካሄዷል።

የኦሮሚያ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሲሳይ ገመቹ በክልሉ ከ10 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የቡልቡላ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክና ሌሎች ስድስት መጋቢ ኢንዱስትሪዎች በግንባታ ላይ ናቸው ብለዋል ።

በሻሸመኔ፣ ዶዶላ፣ ባሌ ሮቤ፣ ኢተያ፣ መቂና አርሲ ነገሌ እየተገነቡ ያሉት መጋቢ ኢንዱስትሪዎች ምርትን በቀጥታ ከአርሶ አደሩ በመረከብ ወደ ቡልቡላ የተቀናጀ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚያስገቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ኢንዱስትሪዎቹ ማምረት ሲጀምሩ ከ100 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥሩ አቶ ሲሳይ ገልጸዋል።

በቡልቡላ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ሁለት ኩባንያዎች ገብተው የማሽን ተከላ ስራ እያከናወኑ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በተለይም ወደ ኢንቨስትመንት የተሸጋገሩ አርሶ አደሮችና ማህበራት ወደ ፓርኩ ገብተው እንዲያለሙ የማበረታታት ስራ እንደሚሰሩም አመላክተዋል።

የኦሮሚያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ አበበ ድሪባ ለኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚቀርቡ የግብርና ግብዓቶችን በጥራትና በብዛት ለማምረት ከኮርፖሬሽኑ ጋር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሩ ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ በጥራት እንዲያለማ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የሚሰጡ 103 ማዕከላት መደራጀታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.