Fana: At a Speed of Life!

200 ከፍተኛ የማደግ ብቃት ያላቸው የንግድ ፈጠራ ሀሳቦችን ለማብቃት ውድድር ተዘጋጀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀጣይ ሦስት ዓመታት 200 ከፍተኛ የማደግ ብቃት ያላቸው የንግድ ፈጠራ ሀሳቦችን ለማብቃት ዓላማው ያደረገ አገር አቀፍ የሥራ ፈጠራ ሀሳብ ውድድር መርሃግብር የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን ጋር በትብብር አዘጋጀ፡፡

ብሩህ የሥራ ፈጠራ ሀሳቦች ውድድር  በሀገሪቱን በተለያዩ ዘርፎች የተለያዩ  ቁልፍ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ አዳዲስ ሀሳቦችን የሚያፈልቁና ለብዙ ዜጎች የሥራ ዕድል  የሚፈጥሩ ወጣቶችን ለማበረታታትና ዕድል ለመስጠት የተዘጋጀ ዓመታዊ ውድድር ነው ተብሏል።

መርሃ ግብሩ በወጣቶች የሚመሩ ኢንተርፕራይዞችን ለመፍጠርና ለማብቃት ለሚቀጥሉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት የሚቀጥል ሲሆን የስልጠና፣ የመነሻ ገንዘብና ጠንካራ የንግድ ልማት አገልግሎት በመስጠት የበቁ እንዲሆኑ የማድረግ ዓላማ ያነገበ ነው።

በተጨማሪም ከ5 እስከ 10 ዓመታት ውስጥ አድገው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚሆኑና ኢትዮጵያን የሚያስጠሩ ድርጅቶች ሊመሰርቱ የሚችሉ፣ ለብዙዎች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ እንዲሁም ለሌሎች ተምሳሌት የሚሆኑ የንግድ ፈጠራ ሀሳብ ያላቸውን ወጣቶች ለማፍራት መሆኑም ተጠቁሟል።

ውድድሩ የሀሳቦች እንደመሆኑ መጠን የማሰልጠን፣ የመሸለምና የማብቃት ሶስት ደረጃዎች ይኖሩታል።

በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታትም 500 ሀሳቦችን በመመልመል ልዩ ልዩ እውቀትና ልምድ ባላቸው አሰልጣኞች ለአንድ ወር በአንድ ቦታ በማሰልጠንና በማወዳደር በውድድሩ መስፈርት መሰረትም አሸናፊ ለሚሆኑት 300 ሀሳቦች የሥራ ማስጀመሪያ ማበረታቻ ሽልማትን ይሰጣል ከኮሚሽኑ ያገኘኘው መረጃ ያመለክታል።

ከተሸለሙት 300 ሀሳቦች 200 ወደ ንግድ ሀሳብ ማጎልበቻ ፕሮግራም ይገባሉም ተብሏል።

በዚህ ውድድር የሚበለጽጉ ጀማሪ የንግድ ሀሳቦችን በቀጥታ የንግድ ልማት አገልግሎት ድጋፍ ከሀሳብ ማጎልበት እስከ ማቋቋም ድረስ ይሰጣቸዋል። የፉክክር መንፈስ በማሳደርም የሚተገበሩ እና ወደ ገበያ ዘልቀው ሊገቡ የሚችሉ እንዲሁም በትንሽ ጊዜ ውስጥ ገቢን የሚያስገኙ ድርጅቶችን ይፈጥራሉ፡፡

ለዚህ ውድድር አመልካቾችን የመሰብሰብ ሥራ በሁሉም የአገራችን ክፍሎች የሚከናወን ሲሆን ቀጣይ ውድድሩና የስልጠናውና የማብቃት ፕሮግራሞች በማዕከላዊነት በአዲስ አበባ እንደሚካሄዱ ተነግሯል።

በ2013 በጀት ዓመት በመጀመሪያው ዙር 50 የንግድ ሀሳቦች ሰልጥነውና ተወዳድረው 30 የሚሸለሙ ሲሆን፤ 20 ደግሞ  ወደ ማጎልበቻ ፕሮግራሙ የሚገቡ ይሆናል።

በተቀመጠው መርሃ ግብር የመጀመሪያው ዓመት ውድድር ምዝገባ ከጥር 1 እስከ ጥር 30 ቀን 2013 ዓ.ም www.bruh-et.com የማመልከቻ ቅፅ በመሙላት ወይም ማመልከቻቸውን በአካል በአቅራቢያቸው ባለ የከተማ የሥራ ዕድል ፈጠራ ቢሮ በማስገባት ማመልከት ይችላሉ ተብሏል።

የሀሳብ አመንጪዎች ኢትዮጵያዊያን መሆን ያለባቸው ሲሆን የሚወዳደሩበት የንግድ ኃሳብም በኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጻሚ ለመሆን መታቀድ እንደሚኖርበት ተነግሯል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.