Fana: At a Speed of Life!

ከተማ አስተዳደሩ የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ለ120 ነዋሪዎች 25 ቤቶችን አስረከበ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 26፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ለ120 ነዋሪዎች 25 ቤቶችን አስረከበ፡፡

ቤቶቹን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ለ120 ነዋሪዎች የተገነቡትን 25 ቤቶችን አስረክበዋል፡፡

ቤቶቹ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ጨርቆስ በሚባለው አከባቢ ለመኖር አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ለነበሩ አቅመ ደካማ ነዋሪዎች ኮንትራክተሮችን በማስተባበር የተገነቡ ናቸው፡፡

ኢንጂነር ታከለ ኡማ ቤቶቹን ባስረከቡበት ወቅት የከተማ አስተዳደሩ ለኑሮ ምቹ የሆኑ የመኖሪያ መንደሮችን በሁሉም የኑሮ ደረጃ ላይ ላሉ ነዋሪዎች የማቅረብ ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

ኢንጂነር ታከለ ቤቶቹን የገነቡ ኮንትራክተሮችን ያመሰገኑ ሲሆን ከሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን መኖሪያ ቤቶቹን ጎብኝተዋል፡፡

የመኖሪያ ቤቶቹ በቂ የንጹህ ውሃ አቅርቦትን ጨምሮ የመጸዳጃ ቤቶች እና የጋራ የማብሰያ ስፍራን ያካተተ መሆኑን ከአስተዳደሩ ከንቲባ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.