Fana: At a Speed of Life!

ወሎ ዩኒቨርሲቲ በ335 ተማሪዎች፣ የአስተዳደር ሰራተኞችና መምህር ላይ እርምጃ ወሰደ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ወሎ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ስራውን አውከዋል ባላቸው 335 ተማሪዎች፣ የአስተዳደር ሰራተኞችና መምህራን ላይ እርምጃ መውሰዱን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁን ተናገሩ።

ፕሬዚዳንቱ በዩኒቨርሲቲው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብሔርና በኃይማኖት ሽፋን በተፈጠረ አለመረጋጋት የመማር ማስተማር ስራው ባለፉት ወራት ውስጥ ለሶስት ጊዜ መቋረጡን አስታውሰዋል።

በዩኒቨርሲቲው ተፈጥሮ በነበረ አለመረጋጋትም የሁለት ተማሪዎች ህይወት ማለፉንና በተወሰኑት ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት መድረሱን አንስተዋል።

ባለፉት ሁለት ወራት ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በመሆን ችግር ፈጣሪዎችን ለመለየት በተከናወነው ጠንካራ የህግ ማስከበር ስራ፥ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራው እንዳይቀጥል ፍላጎት ያላቸውን 332 ተማሪዎች፣ ሁለት የአስተዳደር ሰራተኞችና አንድ መምህር ላይ እርምጃ መወሰዱን አስታውቀዋል።

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ ከዚህ ውስጥ 12 ተማሪዎችና ሁለት የአስተዳደር ሰራተኞች በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየታየ ይገኛል።

ከዚህ ባለፈም አንድ መምህር ከስራ መታገዱን ጠቅሰው፥ ለ320 ተማሪዎች ደግሞ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።

እርምጃ የተወሰዳባቸው ተማሪዎች፣ የአስተዳደር ሰራተኞችና መምህሩ በዩኒቨርሲቲው ውስጥና ውጭ ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር ምክንያት ሆነው መገኘታቸው በማስረጃ መረጋገጡንም ተናግረዋል።

በቀጣይ በድርጊቱ የተሳተፉ ሌሎች አካላትን ለመያዝ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፥ የዩኒቨርሲቲዉን ደንብና መመሪያ በማስተግበር የህግ የበላይነት እንዲከበር በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አውስተዋል።

የመማር ማስተማር ሂደቱን ሰላማዊ ለማድረግ ከደሴ ከተማ፣ ደቡብ ወሎና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አመራሮች፣ የኃይማኖት መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ጋር ውይይት እየተደረገ ነውም ብለዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር አበራ አሉላ በበኩላቸው፥ በዩኒቨርሲቲው ችግር የሚፈጥሩ ተማሪዎችንና ሰራተኞችን ለመያዝ አስተዳደሩ ከህብረተሰቡ ጋር የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በተመሳሳይ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሂደትን አስተጓጉለዋል በተባሉ 18 ተማሪዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ዓለም አቀፍና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደቻሳ ጋንፉሬ እንደገለጹት፥ የተቋሙ ሴኔት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በዩኒቨርሲቲው በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ውስጥ ተሳትፎ ነበራቸው ባላቸው 18 ተማሪዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ውሳኔ አሳልፎአል፡፡

በዚህም ሁለት ተማሪወች ሙሉ በሙሉ ከትምህርታቸው ሲታገዱ፥ ሰባት ተማሪዎች እያንዳንዳቸው ለሶስት ዓመትሠ፣ ስምንቱ ደግሞ ለሁለት ዓመት ከትምህርታቸው እንዲታገዱ ተወስኗል ነው ያሉት።

ከዩኒቨርሲቲው ተሰናብቶ የነበረ አንድ ተማሪ ተመልሶ በተፈጠረው ችግር ውስጥ ተሣትፎ በመገኘቱ በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ክስ እንደተመሰረተበት አቶ ደቻሳ ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ 69 ተማሪዎች የፈጠሩት የስነ ምግባር ችግር ተጣርቶ በሂደት እንደ ጥፋታቸው እርምጃ እንዲወሰድባቸው መወሰኑንም አመልክተዋል፡፡

ምንጭ ፦ ኢዜኣ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.