Fana: At a Speed of Life!

የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ዘመናዊ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ክልል ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የወሳኝ ኩነት ምዝገባ የበለጠ ዘመናዊ እንዲሆን ኮምፒዩተራይዝድ የማድረግ ስራ ታስቦ እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ክልል ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

ከወሳኝ ኩነት ምዝገባ የሚመነጩ ማስረጃዎችን ከተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ፍላጎት ጋር ለማስተሳሰር የደቡብ ክልል ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጄንሲ ከተለያዩ ተቋማት ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።

የክልሉ ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጄንሲ አዋጅ ቁጥር 760/2004 መነሻ በማድረግ በክልሉ ደንብ ቁጥር 114/2006 ተቋቁሞ ከሀምሌ 30/2008 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ምዝገባ ስራ ገብቷል፡፡

በዚህም የተጣለበትን ተልዕኮ ለማስፈጸም የሚያስችሉ በርካታ የአቅም ግምባታ ስልጠናዎችንና የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በየደረጃው ለሚገኙ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ባለሙያዎች፣ ለክብር መዝገብ ሹሞችና ለባለድርሻ አካላት ሲሰጥ ቆይቷል።

በተጨማሪም የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ሽፋንን ለማሳደግና የምስክር ወረቀት የመጠቀም ፍላጎት እንዲጨምር ለማድረግ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅታዊ አሰራር በመፍጠር በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛልም ነው የተባለው።

በመሆኑም ከወሳኝ ኩነት ምዝገባ የሚመነጩ ማስረጃዎችን ከመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ ከፋይናንስ ተቋማትና ከተለያዩ አደረጃጀቶች አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በማቀናጀት እያንዳንዱ ዜጋ እነዚህን ማስረጃዎች እንዲጠቀም የሚያደርግ ተነሳሽነት መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ ተነግሯል፡፡

የደቡብ ክልል ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጄንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ደምስስ ገብሬ ስርዓቱ የበለጠ ዘመናዊ እንዲሆን ኮምፒዩተራይዝድ የማድረግ ስራ ታስቦ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በመድረኩ የክልሉ ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጄንሲ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ አጋፋሪ ይህ የዘመናዊነት መገለጫ የሆነው ስርዓት ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ የሚያስፈልገውን ያክል አለማደጉን ገልፀዋል።

በሻሸመኔ ከተማ በተዘጋጀው መድረክ የማህበራዊ ዋስትና ተቋማት፣ የፍትህ ተቋማት፣ የፋይናንስ ተቋማትና የትራንስፖርት ተቋማት ተገኝተው ተወያይተዋል።

በመለሰ ታደለ

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.