Fana: At a Speed of Life!

ፍርድ ቤቶች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል ድጋፍ ይደረጋል — ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ

አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2013 (ኤፍቢሲ) በየደረጃው የሚገኙ ፍርድ ቤቶች ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል ድጋፍ እንደሚደረግ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ ገለጹ።

ወይዘሮ መዓዛ ዛሬ በአማራ ክልል በመገኘት የፍርድ ቤት የሥራ እንቅስቃሴ ጉብኝትና ከዘርፉ አካላት ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት እንዳሉት ፍርድ ቤቶች የህግ የበላይነት እንዲከበርና ፍትህ እንዲረጋገጥ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።

ፍትህ ፈላጊውን ህብረተሰብ ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን ያህል ወደ ፍትህ መድረስ ያልቻሉ በርካታዎች መሆናቸውን የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በቅርቡ ይፋ ያደረገው ጥናት ማረጋገጡን ጠቅሰዋል።

ይህንን ችግር ለማቃለል የፍርድ ቤቶችን አቅምና ተደራሽነት ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል።

ሁሉም ጉዳይ በፍርድ ቤቶች መልስ ለማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ የሰዎችን መብት በማይነካ ሁኔታ ቀለል ያሉ ጉዳዮችን ከፍርድ ቤት ውጪ ሊታዩ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻት ይኖርብናል ብለዋል።

የህግ የበላይነት ከሌለ ሠላምም ሆነ የምናስበውን ልማት ማረጋገጥ አንችልም ያሉት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቷ፤ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥና ፍትህ እንዲሰፍን ሁሉም በትኩረት ሊሰራ  እንደሚገባ ተናግረዋል።

በሀገሪቱ  እስካሁን ለፍርድ ቤቶች የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይ ይህን ችግር እየተካሄደ ባለው የፍርድ ቤቶች ሪፎርም ይፈታል ብለዋል።

በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተገኝተው ባደረጉት ጉብኝት ለስራ አመቺ ሆኖ እንዳላገኙት ጠቅሰው፤ ፍርድ ቤቱ ራሱን የቻለና ለችሎት ማስቸያ የሚሆን ቦታ ሊኖረው እንደሚገባ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በተለይ በቦታ ጥበት ምክንያት በየኮሪደሩ የሚገኙ የተዘጉ ፋይሎችን ከክልሉ መንግስት ጋር በመነጋገር ፋይሎቹ በአግባቡ የሚያዙበት ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚያስፈልም ጠቁመዋል።

እስካሁን የምናደርገው የበጀት ድጎማ አነስተኛ ቢሆንም በቀጣይ የተሻለ የድጎማ በጀት እንዲኖር፣ የኮምፒዩተርና ሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፍ ለማድረግም ዝግጁ ነን ብለዋል።

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት አቶ አብዬ ካሳሁን በበኩላቸው ፕሬዚደንቷ ያሉብንን ችግሮች ለማየትና በቀጣይ ችግሩን ለመፍታት በመምጣታቸው ሊመሰገኑ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።

ፍርድ ቤቶች ለአንድ ሀገር የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ ሚናን የሚጫወቱ፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲረጋገጡና ልማት እንዲፋጠን ሚናቸው የጎላ እንደሆነ ተናግረዋል።

የጉብኝቱ ዓላማም የፌዴራልና  ክልል ፍርድ ቤቶች በህገ-መንግስቱ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በጋራ ለመወጣት ያሉትን ችግሮች በአካል ተገኝተው በማየት ተደጋግፈው  በጋራ ለማቃለል እንደሆነም አስረድተዋል።

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ በቆይታቸው የክልሉን ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የባህር ዳርና አካባቢው ከፍተኛ ፍርድ ቤት የጎበኙ ሲሆን ከዳኞችና አመራሮች ጋርም መወያየታቸውን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በክልሉ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት እስከ ንዑስ ወረዳ ድረስ 209 ፍርድ ቤቶች ለህብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙም ከክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.