Fana: At a Speed of Life!

አዲስ ወግ አንድ ጉዳይ የውይይት መድረክ ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 27 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ ወግ አንድ ጉዳይ የውይይት መድረክ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ተካሂዷል፡፡
መድረኩ “የኮሙዩኒኬሽን መንገዶቻችን ለምርጫ ሰላምና ደኅንነት” በሚል ርዕስ ነው የተካሄደው፡፡
በስነ አዕምሮ ህክምና ባለሙያው ዶክተር ምህረት ደበበ አወያይነት፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ ጥበባት ኮሌጅ ዲን ዶክተር ዕዝራ አባተ፣ የኬሚካል መሐንዲስ ኢንጂነር ጌታሁን ሔራሞ እንዲሁም መምህርትና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ድጋፍ ሰጪ ቢሮ ዳይሬክተር ዶክተር አጋረደች ጀማነህ አማካኝነት ውይይቱ ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ ላይ ስነ ጥበብ ሀሳብን በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚመች ተነስቷል፡፡
በጥበቡ ዓለም ጥበባቸውን ለጥቅም ብለው ለአሉታዊ ዓላማ የሚያውሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ህዝብን ለመጥቀም አስበው የሚተጉ ባለሙያዎች እንደሚገኙም ነው የተነሳው።
የስነ ጥበብ ባለሙያዎች ሥራዎቻቸውን ኅብረተሰቡ በሚረዳው መንገድ ቢያቀርቡ ተግባቦት ውጤታማ እንደሚሆንም ተወያዮቹ ገልጸዋል።
ስነ ጥበብ በየትኛውም ሁኔታ ግጭትን በማብረድ ወደ ኅብረት ለማድረስ፣ ለማነቃቃት እና ለማንቀሳቀሰስ፣ በግጭት አልባ መንገድ የሀሳብ ተቃርኖን ለመግለጽ ዓይነተኛ መሣሪያ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡
ቀለም ቅቡልነትን ከሚወስኑ ጉዳዮች አንዱ ነው መሆኑም ተነስቷል። ቀለም ተያያዥ ስሜቶችን የሚፈጥር ሲሆን÷ ሰዎች ስለነባራዊ ሁኔታ ሰፊውን መረጃ የሚያገኙት በማየት ነው ተብሏል።
ስለዚህ የምርጫ ምልክቶችን ጨምሮ ልዩ ልዩ ሀገራዊ ጠቀሜታ ያላቸው ትዕምርቶች የሰውን ስነ አዕምሮ በመረዳት ሊዘጋጁ ይገባልም ነው የተባለው።
ከዚህ ባለፈም በመድረኩ ላይ የቡድን ማንነት ያለው ማኅበረሰብ ቢኮንም፣ ምርጫ የግል ውሳኔ በመሆኑ የግለሰብ ነጻነትን ማበረታታት ተገቢ መሆኑ ተነስቷል።
ፓርቲ እና አስተዳደር ቢቀየርም ሀገር እና መንግሥት የሚቀጥሉ መሆኑን በመገንዘብ ለጊዜያዊው ዘላቂውን ላለማጥፋት መጠንቀቅ ያስፈልጋልም ነው የተባለው።
ተግባቦት ስኬታማ የሚሆነው መግባባት፣ መናበብ፣ ትክክለኛ የትርጓሜ አረዳድ፣ ሀሳብን በአግባቡ መግለጽ ሲታከሉበት ነው ተብሏል።
መገናኛ ብዙሀን ተደራሽ የሚያደርጉት ብዙሀኑን ማኅበረሰብ እንደ መሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባልም ነው የተባለው።
በመሆኑም ተግባቦት ውጤታማ እንዲሆን፣ መገናኛ ብዙሀን ተደራሾች ለማድመጥ በሚቀላቸው መንገድ አግባብ ያለው ይዘትን ሊያዘጋጁ ያስፈልጋል ተብሏል።
ህዝቡ የሚፈልገውን ፓርቲ ያለ ምንም ሁከት እና መንገላታት ለመምረጥ እንዲችል የጸጥታ አካላት ሚናቸውን በመገንዘብ ከቅድመ ምርጫ እስከ ድህረ ምርጫ ላለው ሁኔታ በዝግጅት ላይ እንደሚገኙም ነው የተገለጸው።
በዚህም በምርጫው ሂደት በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የሚሠማራ የፖሊስ ሀይል ገለልተኛ እንዲሆኑ ስልጠና እና ሌሎች ተግባራት እየተከወኑ እንደሚገኙም ተነስቷል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.