Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ የአከራካሪ የምርጫ ጉዳዮች በፍርድ ቤት ስለሚስተናገዱበት አግባብ የተዘጋጀ ረቂቅ ደንብን ለዝርዝር ዕይታ መራ

አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2013 (ኤፍቢሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአከራካሪ የምርጫ ጉዳዮች በፍርድ ቤት ስለሚስተናገዱበት አግባብ ላይ የተዘጋጀ ረቂቅ ደንብን ለዝርዝር እይታ ለህግና ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መራ፡፡

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ረቂቅ ደንቡ ምርጫው ፍትሃዊ እንዲሆን የራሱን ሚና መጫወት የሚችል በመሆኑ ለተጨማሪ ዝርዝር ዕይታ ለቋሚ ኮሚቴው መርቶታል፡፡

በረቂቅ ደንቡ ላይ ከምርጫ ሂደት ጋር በተያያዘ የሚቀርቡ አቤቱታዎች እና ክርክሮች ለመምራትና ለማስተናገድ የሚያስፈልጉ ስነስርአቶችም መካተታቸው ተጠቅሷል፡፡

የምርጫ ጉዳዮች የሚያስተናግዱ ፍርድ ቤቶች ጉዳዮችን ፈጣን፤ ግልጽና ተዓማኒ በሆነ መልኩ ማስተናገድ እንዲችሉ ተደርጎ መዘጋጀቱም ተነስቷል።

የመራጮች ምዝገባ አቀራረብና ውሳኔ አሰጣጥ ስነስርዓት ላይም መራጭ ለመመዝገብ ያለአግባብ ተከልክያለሁ ብሎ ቅሬታ ሲያቀርብ የምርጫ ክልሉ በ5 ቀን ምላሽ ሳይሰጠው ከቀረ ወይም በምላሹ ቅሬታ ከገባ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከሆነ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲሁም በክልል ከሆነ ደግሞ ለወረዳ ፍርድ ቤቶች በ5 ቀናት ውስጥ አቤቱታውን እንዲያቀርብ ይፈቅዳል።

ይህ ሂደት በመራጭነት መመዝገብ የሌለበት ሰው ያለአግባብ ተመዝግቧል የሚል ቅሬታ ሲፈጠር በተመሳሳይ ሂደት ተፈጻሚ ይሆናል፤ ፍርድ ቤት ተከራካሪዎችን ከመረመረ በኋላም በአራት ቀናት ውሳኔ እንደሚሰጥ ያትታል።

አመልካቹ አቤቱታውን ካቀረበ ጊዜ ጀምሮ ባሉት 10 ቀናት ውሳኔ መስጠት እንዳለበት ረቂቁ ይደነግጋል።

ፍርድ ቤቱ የምርጫ ጣቢያ ወይም የምርጫ ክልሉ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ የሰጠውን ውሳኔ የሻረው እንደሆነ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የጸና ይሆናል።

በረቂቅ ደንቡ አቤቱታ ስለሚቀርብባቸው ምክንያቶች ላይ ከአዋጁ ውጪ በእጩነት ከመመዝገብ መከልከል፤ ኢትዮጵያዊ ዜጋ አይደለም በሚል፤ በምርጫ ክልሉ የኖረው ከአንድ ዓመት በታች ነው ወይም በእጩነት ሊቀርብበት በፈለገው ቦታ አልተወለደም በሚል፣ ሊወዳደርበት የፈለገበት ቦታ በስራ ላይ የቆየው ከ2 ዓመት በታች ነው በሚል፣ በፍርድ ወይም በህግ የመመረጥ መብት የተገፈፈ ከሆነ የሚልና መሰል የቅሬታ ማቅረቢያ ምክንያቶች ማካተቱ ነው የተገለጸው።

በሌላ በኩል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው መደበኛ ስብሰባው ከዓለም አቀፍ የልማት ማህበር ለሴቶች ኢንተርፕርነርሽፕ ልማት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የተገኘውን ተጨማሪ የብድር ስምምነት በስድስት ተቃውሞ አብላጫ ድምጽ አጽድቆታል።

የ100 ሚሊየን ዶላር የብድር ስምምነቱ ከወለድ ነጻና የ6 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ38 ዓመት ውስጥ ተከፍሎ ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡

የምክር ቤት አባላቱ መንግስት ለልማት ባንክ በ3 በመቶ ወለድ ቢሰጥም ልማት ባንክ ለማይክሮ ፋይናንሶች በ6 በመቶ ማይክሮ ፋይናንሶች ደግሞ በ18 በመቶ ወለድ ለተጠቃሚዎቹ ማውረዱ ጫናው ተጠቃሚዎች ላይ ይሆናል የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡

በተሰጠው ምላሽም ገንዘቡ ከተጠቃሚ የሚሰበሰበው በረጅም ጊዜ ብድር ሲሆን ለአበዳሪው ግን በውጪ ምንዛሬ የሚመለስ በመሆኑ በጊዜው ልዩነት የውጪ ምንዛሬው ልዩነት መፍጠሩ አይቀርም ተብሏል።

ምክር ቤቱም በቀጣይ የፋይናንስ ስርዓቱ እንዲታይ በማሳሰብ በ6 ተቃውሞ በ9 ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል፡፡´

ሀይለኢየሱስ ስዩም

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.