Fana: At a Speed of Life!

የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ውጤታማነት የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲቲዩት እንዲከታተል ስምምነት ላይ ተደረሰ

የአዲስ አበባ ፣ ጥር 28 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም ሂደቱን በብቃት ለመከታተልና ውጤቱን ለመገምገም የሚያስችል የትብብር የመግባቢያ ሰነድ የገንዘብ ሚኒስቴር እና የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲቲዩት ጋር ተፈራረሙ፡፡

በስምምነቱ መሰረት የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲቲዩት የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አፈጻጸም ላይ ክትትልና ግምገማ በማድረግ ስለአፈጻጸሙ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ወቅታዊ መረጃ እንዲኖር ያስችላል ተብሏል፡፡

ኢንስቲቲዩቱ በበቂ ትንተና እና ጥናት ላይ ተመስርቶ የሚያቀርበው ግብአት ለገንዘብ ሚኒስቴር እና ለሌሎች አስፈጻሚ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የኢኮኖሚ ማሻሻያው ስላመጣው ለውጥ መረጃዎችን ለፖሊሲ ግብዓትነት ያመነጫልም ነው የተባለው፡፡

በስምምነቱ መሰረት ኢንስቲቲዩቱ በተለይም የኢኮኖሚ ማሻሻያው የማክሮ ኢኮኖሚክ፣ መዋቅራዊና የዘርፍ ዕቅዶች ማለትም ግብርና፣ ማምረቻ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም እና ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጅ በጥልቀት በመተንተንና ያለፈውን ዓመት አፈጻጸም በመገምግም ለቀጣይ ስራ ጠቃሚ ምክረ ሃሳቦችን እንደሚያቀርብ ተነግሯል፡፡

በተጨማሪም ኢንስቲቲዩቱ በማሻሻያው ቅድሚያ በተሰጣቸው ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ማለትም የንግድ ሚዛን ጉድለት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የዋጋ ንረገት፣ የፈሲካል ፖሊሲ፣ የእዳ ጫና እና የስራ ዕድል ፈጠራ ዙሪያ ጥልቅ የሆኑ የፖሊሲ ትንተናዎችን ያካሂዳል፡፡

ከእነዚህ ተግባራት ባሻገርም ስለ ገንዘብ ተቋማት ተደራሽነት፣ ለንግድና ኢንቨስትመት ስራዎች ምቹ ሁኔታዎችን ስለመፍጠር፣ ስለሎጅስቲክስ ቅልጥፍና የኃይል ልማትና አቅርቦት የትንተና ስራዎችን ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሷል፡፡

መንግስት ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ፕሮግራም በመቅረፅ የማክሮ ኢኮኖሚ፣ የመዋቅራዊ ለውጥና የሴክተር ማሻሻያ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና የፕላንና ልማት ኮሚሽን የዚህ ፕሮግራም የማከሮ ኢኮኖሚ፣ መዋቅራዊና የዘርፍ ማሻሻያ ቁልፍ አስተባባሪ አካላት ናቸው ተብሏል፡፡

ማሻሻያው ሁሉን አቀፍ በመሆኑና ከአስፈጻሚ ተቋማት ስፋት የተነሳም በግብ የተያዙትን ውጤቶች በተከታታይነት መገምገምና መተንተን አስፈላጊ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የኢፌዴሪ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲቲዩት በጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም.የተቋቋመ ሲሆን ትኩረቱን በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ በማድረግ ለመንግስት ውሳኔዎች ጠቃሚ የሆኑ ግብአቶችን የሚሰጥ ተቋም ነው፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.