Fana: At a Speed of Life!

በቴሌኮም መሠረተ ልማት ላይ በደረሰ አደጋ 100 ሚሊየን ብር የሚገመት ኪሳራ መድረሱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 30፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም በመሠረተ ልማቶች ላይ በደረሰ አደጋ 100 ሚሊየን ብር የሚገመት ኪሳራ መድረሱን ገለጸ።

ኢትዮ ቴሌኮም በመሰረተ ልማቶች ደህንነት ዙሪያ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በአዲስ አበባ እየተወያየ ነው።

በውይይቱ ከ20 እስከ 30 ዓመት እንዲያገለግሉ የተዘረጉ የፋይበር እና የኮፐር ኬብል ኔትወርክ መሰረተ ልማቶች በስርቆት፣ በቃጠሎ እና በመቆራረጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ እየወደሙ መሆኑን አስታውቋል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ፥ የጉዳቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣት ተቋሙ የአገልግሎት አሰጣጡን በጥራት እንዳያቀርብ እና ተደራሽነቱን እንዳያሰፋ እየተፈታተነው መሆኑን ተናግረዋል።

ባለፉት 6 ወራት ብቻ በሀገር አቀፍ ደረጃ በመሰረተ ልማቶች ላይ 547 አደጋዎች መድረሳቸውን የገለጹት ዋና ስራ አስፈፃሚዋ፥ ከዚህ ውስጥም 90 በመቶ የሚሆኑት በግዴለሽነት የተፈጸሙ መሆናቸውን አንስተዋል።

እንዲሁም ከ46 በመቶ በላይ የሚሆኑት ጉዳቶች ሆን ተብለው የሚፈጸሙ መሆናቸው ተረጋግጧል ነው ያሉት።

በመሰረተ ልማቶች ላይ በደረሱ ጉዳቶች ምክንያትም ድርጅቱ ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ለሆነ ኪሳራ መዳረጉንም አስረድተዋል።

ይህም 25 የሞባይል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎችን መክፈት የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

የደረሰው ጉዳት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ34 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል።

በቀጣይ የሚደርሰውን ጉዳት ለማስወገድም ህብረተሰቡ እና የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን የመከላከል ስራ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል ።

 

በበላይ ተስፋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.