Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል የጤና አገልግሎቶችን የማስቀጠልና ድንገተኛ ምላሽና ድጋፍ የመስጠት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2013 (ኤፍቢሲ) የጤና ሚኒስቴር ከተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ አጋር አካላት እንዲሁም ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በመቀናጀት በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች እየተሰጠ ያለውን የድንገተኛ ምላሽና የጤና አገልግሎት ድጋፍ አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

በቅርብ ጊዜ ከተላከው ከ71 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ መድሃኒቶችና የህክምና ግብዓቶች ጨምሮ በመድሃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ የመቀሌ እና ሽሬ ቅርንጫፍ በአጠቃላይ ግምታቸው ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ መድሃኒቶች እና የህክምና ግብዓቶች በክምችት የሚገኙ ሲሆን በየቀኑ ወደ ተለያዩ የክልሉ ወረዳዎች ለሚገኙ ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች እየተሰራጩ እንደሚገኙ ሚኒስትሩ ገልጿል፡፡

በተጨማሪም ግምታቸው 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚሆኑ የተለያዩ ክትባቶች የተሰራጩ ሲሆን በጤና ሚኒስቴር 12 አምቡላንሶች፣ 11 ለቢሮና ለመድሀኒት ማጓጓዣ አገልግሎት የሚውሉ ፒካፕ መኪኖች፣ 1 የቅዝቃዜ ሰንሰለት ያለው ተሽከርካሪ ለክልሉ የተላኩ ሲሆን 100 ኮምፕዩተሮች ለክልሉ ተሰጥተዋል፡፡

ለእነዚህ የመልሶ ማቋቋምና አገልግሎቶችን የማስቀጠል ስራዎች 37 ሚልዮን ብር ለክልሉ ጤና ቢሮ የተላለፈ ሲሆን በያዝነው ሳምንት ተጨማሪ በጀት ለማስተላለፍ በሂደት ላይ መሆኑ ነው የተጠቀሰው፡፡

የተለያየ የሞያ ስብጥር ያለው ከጤና ሚኒስትር፤ ከህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት እና ኤጀንሲዎች የተውጣጣ ቡድን ወደ ክልሉ በመሄድ ከክልሉ ጤና ቢሮ እና ከአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ቡድኑ ጋር እየሰራ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡

የኮቪድ ምርመራ እና ህክምና ለማስቀጠል የባለሙያዎች ቡድን ወደ ክልሉ ተልኮ ዳሰሳ ያደረገ ማድረጉም ተነስቷል፡፡

የላቦራቶሪ ምርመራ እና የህክምና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ተጠናቆ በጥቂት ቀናት ውስጥ በመቀሌ ከተማ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተብሏል፡፡

የደም አቅርቦትን ለማጠናከርም 952 ዩኒት ደም ከክልሉ ደም ባንኮች የተሰራጨ ሲሆን 2803 ዩኒት ደም ደግሞ ከመቀሌ የበጎ ፈቃድ ደም ለጋሾች ተሰብስቧል፡፡

ከተለያዩ አጋር ድርጅቶችም የተለያዩ አልሚ ምግቦችና ለሴቶች ንጽህና የሚውሉ ግብዓቶችም ተሰራጭተዋል፡፡

በክልሉ የሚገኙ ጤና ተቋማት በከፊል ስራ ጀምረው ለህብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን  ካሉት ሆስፒታሎች ውስጥ 46 በመቶ የሚሆኑት አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

በቅርብ ጊዜያትም ሁሉም ጤና ተቋማት ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት እንዲሰጡ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ይገኛልም ሲል ነው የጠቀሰው፡፡

ተፈናቅለው በተለያዩ ከተሞች ለሚገኙ ወገኖችም በብሄራዊ አደጋና ስጋት ኮሚሽን ከሚደረገው የምግብ ድጋፍ ጎን ለጎን ተንቀሳቃሽ የህክምና ቡድኖች የህክምናና የስርዓተ ምግብ ድጋፍ በተለይም ተጋላጭ ለሆኑ እናቶችና ህጻናት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

በሚንስትሮች የሚመራው ብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ አስተባባሪ ኮሚቴ በመቀሌ ከተማ ካደረገው ሁለት ዙር ምልከታና ውይይት በተጨማሪ፤ በጤና ሚኒስቴር ከተቋቋመው ግብረ ሃይል ውስጥ በሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ዓለምጸሀይ የተመራ ቡድን ያለውን የመልሶ ማቋቋም ስራዎች በተለያዩ ተቋማት በመዘዋወር መመልከቱን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.