Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋንን 94 በመቶ ለማድረስ እየተሰራ ነው- ዶ/ር  ግርማ አመንቴ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 30 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)  በኦሮሚያ ክልል በቀጣዮቹ 10 ዓመታት የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋንን 94 በመቶ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የኦሮሚያ የግብርናና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ ተናገሩ።

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ጮቢ ወረዳ በ21 ሚሊየን ብር የተገነባው የጮቢ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመርቋል።

በምረቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል የግብርናና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ እንዲሁም የፌዴራልና የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በዚህ ወቅት የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እንዳሉት የጮቢ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ከ21 ሺህ በላይ ዜጎችና በርካታ መንደሮች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስታውቀው በቀጣይ ቀሪ የውሃ ጉድጓዶችን ወደ ስራ በማስገባት በሮጀክቱ 50 ሺህ ዜጎች እንዲጠቀሙ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበትና ገንዘቡ ከልማት አጋሮች፣ ከውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ከውሃ ልማት ኮሚሽን፣ ከኦሮሚያ ክልል፣ ከዞኑና ከወረዳው አስተዳደር የተገኘ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የአካባቢው ማህበረሰብም ለፕሮጀክቱ ግንባታ ሁለት ሚሊየን ብር የሚገመት የጉልበት አስተዋጽኦ ማድረጉን አስታውቀዋል።

በቀጣይም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በአምስት አመት ውስጥ “ውሃ ለሁሉም” በሚል መርሃ ግብር የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ለማዳረስ እየሰራ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኦሮሚያ የግብርና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ በበኩላቸው በኦሮሚያ ክልል በቀጣዮቹ 10 ዓመታት የክልሉን የንጹህ የመጠጥ ውሃ ሽፋን 94 በመቶ ለማድረስ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ለዚህም በክልሉ ተጀምረው የተቋረጡና የተለያዩ መንደሮችን ማዳረስ የሚችሉ ፕሮጀክቶች ላይ በትኩርት እንደሚሰራ አመላክተዋል።

ዶክተር ግርማ አክለውም የጮቢ የውሃ ፕሮጀክት በበርካታ ቀበሌዎች ለሚኖሩ ዜጎች አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች የውሃ መሰረተ ልማቱን በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.