Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮ ቴሌኮም በሰሜን ሪጅን ካሉ ጣቢያዎች ለ365ቱ የሞባይል ድምፅና የመደበኛ ስልክ አገልግሎት ማስጀመሩን ገለፀ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 1 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም በሰሜን ሪጅን ካሉ ጣቢያዎች መካከል ለ365ቱ የሞባይል ድምፅና የመደበኛ ስልክ አገልግሎት ማስጀመሩን ገለፀ ።

ድርጅቱ በሰሜን ሪጅን ያለውን የቴሌኮም መሠረተ ልማት ጥገና እና አገልግሎትን የተመለከተ ዛሬ በማህበራዊ ትስስር ገፁ መግለጫ አውጥቷል።

ኢትዮ ቴሌኮም በሰሜን ሪጅን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ከሌሊቱ 6 ሰዓት ጀምሮ የቴሌኮም አገልግሎት መቋረጡን አስታውሷል።

ይህን ተከትሎ ኩባንያው ታህሳስ 1 ቀን 2013 ዓ.ም በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የቴሌኮም አገልግሎቱ መቼ፣ እንዴት እና በማን እንደተቋረጠ የሚያሳይ በማስረጃ የተደገፈ ዝርዝር ማብራሪያ መስጠቱን ነው የገለፀው።

በመሆኑም በሪጅኑ የተጎዱ መሠረተ ልማቶችን በመጠገን እና የጠፉ የቴሌኮም መሳሪያዎችን በመተካት አገልግሎቱን ወደነበረበት ለመመለስ ከፍተኛ ርብርብና ሰፊ የቅንጅት ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል።

እስካሁን በተጠናቀቁ የጥገናና የሃይል አቅርቦት ስራዎች በሪጅኑ ካሉ ጣቢያዎች መካከል 365ቱን ለአገልግሎት ዝግጁ በማድረግ የሞባይል ድምፅና የመደበኛ ስልክ አገልግሎት መጀመሩ ተገልጿል።

በተጨማሪም በሪጅኑ የሚገኙ ባንኮች አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ቅድሚያ በመስጠት እየተሰራ ነው ተብሏል።

ከመቀሌና አዲግራት በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት በሽሬ እንደስላሰ፣ በአክሱም እና በአድዋ ከተሞችና አካባቢያዎቻቸው የሚገኙ ባንኮች የብሮድባንድ አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል።

በተመሳሳይ ሁኔታ የድርጅት ደንበኞች የብሮድባንድ አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ ቅድሚያ ተሰጥቶ የጥገና ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጿል።

ኩባንያው በአብዛኛዎቹ አካባቢዎች አገልግሎቱን ጊዜያዊ የትራንስሚሽን መስመሮችን በመዘርጋት ያስጀመረ በመሆኑ የአገልግሎት ጥራትና መቆራረጥ ሊያጋጥም ስለሚችል በሪጅኑ ያሉትን የቴሌኮም መሠረተ ልማቶች ሙሉ በሙሉ በመጠገን እና የጎደሉትን በመተካት አገልግሎቱን “በሙሉ አቅም እስከምናስጀምር በትዕግስት እንድትጠብቁን በአክብሮት እንጠይቃለን”ሲል ደንበኞቹን ጠይቋል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.