Fana: At a Speed of Life!

“ስለትግራይ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚቀርቡ ወቀሳዎች በመረጃ ያልተደገፉ ናቸው” – የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2013 (ኤፍቢሲ) የፌዴራል መንግስት በትግራይ ክልል ስላካሄደው የህግ ማስከበር እርምጃ እና ከእርምጃው መጠናቀቅ በኋላ በክልሉ ስላለው አጠቃላይ ሁኔታ በተመለከተ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚቀርቡ ወቀሳዎች በመረጃ ያልተደገፉ መሆናቸውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርዱ ዋና ሰብሳቢ አቶ ለማ ተሰማ አስታወቁ ።

አቶ ለማ ተሰማ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፣ ቦርዱ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች እና አጎራባች የአማራ ክልል አካባቢዎች በሁለት ዙር ተዘዋውሮ ጉብኝት አድርጓል፡፡

እንደ ሰብሳቢው ከሰብዓዊ መብት አያያዝ ጋር በተገናኘ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚቀርቡ ወቀሳዎች በመረጃ ያልተደገፉ ናቸው።

ለእነዚህ አካላት ሀሰተኛ መረጃዎች የሚያቀርቡት የጁንታው ርዝራዦች እንዲሁም ቀደም ሲል በጁንታው ሲረዱ የነበሩ አሁን ደግሞ ጥቅማቸው የተቋረጠባቸው አካላት ይሆናሉ የሚል እምነት እንዳላቸው አስታውቀዋል።

ቦርዱ በባለፉት ጊዜያት በሁለት ዙር ባደረጋቸው የመስክ ምልከታዎች ደካማ ጎኖች ብሎ በለያቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይቷል ያሉት ሰብሳቢው፣ አሁን ችግሮቹ ምን ያህል ተቀርፈዋል የሚለውን በአካል ለማየት የመርማሪ ቦርዱ አባላት በተያዘው ሳምንት ወደክልሉ እንደሚሄዱም ጠቁመዋል።

“በየትኛውም ሀገር ቢሆን ጦርነት ባለባቸው አካባቢዎች የሚኖር ህዝብ ለረሃብ እና ለሌሎችም ማህበራዊ ችግሮች ሊጋለጥ ይችላል” ያሉት አቶ ለማ፣ ከህግ ማስከበር እርምጃው መጠናቀቅ በኋላ በትግራይ ክልል ለሚኖሩ ዜጎች ምግብን ጨምሮ ሌሎች ሰብዓዊ ድጋፎች እየተደረጉ ያሉትም ይህንን ታሳቢ በማድረግ እንደሆነ አመልክተዋል።

በክልሉ ካሉ የማይመቹ ሁኔታዎች አንጻር ለዜጎች እየተደረገ ያለው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት በሚፈለገው ልክ አጥጋቢ ላይሆን ይችላል ያሉት የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ፣ ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚቀርቡ ወቀሳዎች ግን በመረጃ ያልተደገፉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

“በመስክ ጉብኝቱ ወቅት በአካባቢዎች ህዝቡን ስናወያይ እንደተረዳነው የመከላከያ ሰራዊት አባላት በንጹሃን ዜጎች ላይ ጥቃት እያደረሱ እንደሆነ ሲነገር የነበረው ፍጹም የተሳሳተ መሆኑን ተረድተናል” ብለዋል::

የመከላከያ ሰራዊት አባላት ጥቃት አድርሰውብኛል የሚል አንድም ሰው አለማግኘታቸውንም ገልጸዋል።

“የመከላከያ ሰራዊቱ የበቀል ስሜት ቢኖረው ኖሮ ጥቃት ያደረሱበት የህወሓት ተዋጊዎች ላይ እርምጃ መውሰድ ይችል ነበር” ያሉት አቶ ለማ፣ የሰራዊቱ ዋነኛ ዓላማ የህግ የበላይነትን ማስከበር በመሆኑ ጥፋተኞቹ ላይ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ እንደየጥፋታቸው በህግ እንዲዳኙ ለፌዴራል ፖሊስ እያስረከበ ነው ብለዋል።

በህግ ማስከበር እርምጃው ሂደት በቁጥጥር ስር የዋሉ ምርኮኞች እና በሰላም እጃቸውን ለሰራዊቱ የሰጡ የህወሓት አመራሮች እንዲሁም ተዋጊዎች በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን ቦርዱ ከመስክ ምልከታው ማረጋገጥ መቻሉንም አስታውቀዋል::

በህግ ማስከበር ሂደቱ የቆሰሉ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት እና የጁንታው ተዋጊዎች ያለምንም ልዩነት ህክምና እያገኙ እንደሆነም ጠቁመዋል።

የመርማሪ ቦርዱ አባላት በህግ ጥላ ስር ያሉ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮችን ባነጋገሩበት ወቅት ህክምና፣ ምግብ፣ መኝታ እና ሌሎችም አስፈላጊ ነገሮች በአግባቡ እያገኙ እንደሆነ ከአንደበታቸው መስማታቸውን ገልጸዋል::

በህግ ጥላ ስር ከሚገኙት መካከል አንዳንዶቹ “እኛ ጥሩዎች አይደለንም፤ እንደስራችን ቢሆን ኖሮ ይሄ እንክብካቤ አይገባንም ነበር” ሲሉ መስማታቸውንም አስታውሰዋል::

 

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.